ቤኒን እና ማላዊ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ምድብ ለመቀላቀል ይጫወታሉ

በ2015 የሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን እየተደረጉ በሚገኙት የቅድመ-ማጣሪያ ጨዋታዎች ቤኒን እና ማላዊ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። ማላዊ ቻድን፣ ቤኒን ደግሞ ሳኦቶሜ እና ፕሪንስፔ ደሴቶችን በማሸነፋቸው ነው የመጨረሻውን የቅድመ ማጣሪያ ለመቀላቀል የቻሉት።

የማላዊ ብሔራዊ ቡድን ብላንታየር ላይ የቻድ አቻውን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሎ የነበረ ቢሆንም በመልሱ ጨዋታ 3-1 ተሸንፏል። ነገር ግን ከሜዳው ውጪ ባስቆጠረው ግብ አማካኝነት ወደ ሁለተኛው ዙር ለማለፍ ችሏል።

ቤኒን በበኩሉ በጁን 12 ብሔራዊ ስታዲየም ባለሜዳውን የሳኦቶሜ ብሔራዊ ቡድን ለእንግሊዙ ዌስትብሮም በሚጫወተው ስቴፈን ሴሴኞን ግቦች 2-0 መርታት ከመቻሉም በተጨማሪ በመልሱ ጨዋታ 2-0 በማሸነፍ 4-0 በሆነ የድምር ውጤት ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።

በሁለተኛው ዙር ቤኒን እና ማላዊ የሚጫወቱ ሲሆን የሁለቱ አሸናፊ ኢትዮጵያ፣ አልጄሪያ እና ማሊ ወደሚገኙበት ምድብ B ይቀላቀላል። የመጀመርያው ጨዋታ ከሐምሌ 11-13 ባለው የጊዜ ገደብ በቤኒን ዋና ከተማ ኮቶኑ የሚደረግ ሲሆን ከ2 ሳምንት በኋላም የማላዊዋ ብላንታየር የመልሱን ጨዋታ ታስተናግዳለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ከቤኒን ጋር የተገናኘው በ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሲሆን በሜዳው 0-0 ቢለያይም ኮቶኑ ላይ አዳነ ግርማ ባስቆጠረው ግብ አቻ በመውጣት ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሎ ነበር። ከማላዊ ብሔራዊ ቡድን ጋር በ2011ቱ ሴካፋ ለመጨረሻ ጊዜ የተደረገው ጨዋታ ደግሞ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። በዚህም ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ እንደነበር ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *