ባሳለፍነው ማክሰኞ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሐ ጨዋታ የቱኒዚያው ኤስፔራንስን ያስተናገደው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በሜዳ ላይ የቆየው ለ14 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡
ሮበርት ከጉዳቱ በኋላ የህክምና ምርመራ የተደረገለት ሲሆን ጉልበቱ ላይ ያጋጠመው ጉዳት የቀዶ ጥገና እንደሚያስፈልገው ተነግሮታል፡፡ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስም በፍጥነት ከጉዳቱ እንዲያገግም ለማድረግ በሀገር ውስጥ አልያም ከኢትዮዽያ ውጭ ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ለማወቅ ችለናል ።
ሮበርት ከህመሙ አገግሞ መቼ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ክለቡ ያለው ነገር ባይኖርም ከቀዶ ጥገናው ምርመራ በኋላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡ ሮበርት ከደረሰበት ጉዳት አንፃር እስኪያገግም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በቀሩት የፕሪምየር ሊግም ሆነ የካፍ ቻምፒንስ ሊግ ጨዋታ ላይ የመድረሱ ነገር አጠራጣሪ ነው፡፡