ቻምፒየንስ ሊግ | ኤቷል ደ ሳህል እና አል አህሊ ሲያሸንፉ ዛማሌክ ነጥብ ጥሏል

የካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች ማክሰኞ መደረግ ሲጀምሩ ኤትዋል ደ ሳህል እና አል አሃሊ ሶስት ነጥብ ያሳኩበትን ድል ሲያስመዘግቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራንስ፣ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ ከአል ሂላል እና አል አሃሊ ትሪፖሊ ከዛማሌክ በተመሳሳይ ያለግብ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡

 

ምድብ ሀ

 

የሞዛምቢኩ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ ማፑቶ አል ሂላልን ገጥሞ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ፌሮቫያሪዮ በጨዋታው ከሱዳኑ ተጋጣሚው የተሻለ የነበረ ቢሆንም የአጨራረስ ድክምት ሶስት ነጥብ እንዳያገኙ አግዷቸዋል፡፡ አል ሂላል ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ለማጠናቀቅ ተገዷል፡፡

ኦምዱሩማን በተደረገው እና ላይ ከፍተኛ ግምትን ያገኘው የኤል ሜሪክ እና ኤትዋል ደ ሳህል ጨዋታ በሶሱ ክለብ የ2-1 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡ ኤትዋል ከወዲሁ ወደ ሩብ ፍፃሜ የሚያደርገውን ጉዞ ያሳመረ ውጤትን ከሱዳን ይዞ ተመልሷል፡፡ ብራዚላዊው ድያጎ አኮስታ ሃምዛ ላህማር ያሻገረውን የቅጥታ ምት ኳስ በግንባሩ በመግጨት በ33ኛው ደቂቃ ኤትዋልን ቀዳሚ ሲያደርግ ሱዳናዊው አጥቂ ባክሪ አል መዲና ሜሪክ ከእረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ አቻ አድርጓል፡፡ ከፍተኛ ፉክክር እና ከረጅም ርቀት የሚሞከሩ ሙከራዎች በተያበት የሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሊገባደድ ሽርፍራፊ ሰኮንዶች በቀሩበት ሁኔታ ላይ ተቀየሮ ወደ ሜዳ የገባው አልጄሪያዊው ሃሚር ቦአዛ የኤትዋልን የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ኤቷዋል በስድስት ነጥብ ምድቡን ሲመራ በአራት ነጥብ የሚያንሰው አል ሂላል ሁለተኛ ነው፡፡

ምድብ ለ

በገለልተኛ ሜዳ ሴፋክ ላይ ዛማሌክን ያስተናገደው አል አሃሊ ትሪፖሊ ከዛማሌክ ጋር 0-0 ተለያይቷል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙኤድ ኤላፊ የሞከረው ሙከራ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት በሁለተኛው አጋማሽ ስታንሊ ኦዋውቺ ዛማሌክን ቀዳሚ ሊያደርግበት የሚችልበትን እድል መሃመድ ናሽኖሽ አምክኖበታል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ዛማሌክ በአራት ነጥብ ምድቡን ይመራል፡፡ ዛሬ ሃራሬ ላይ ካፕስ ዩናይትድ ዩኤስኤም አልጀርን ያስተናግዳል፡፡

 

ምድብ ሐ

 

አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤስፔራንስ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ሳቢ ያልነበረው እና ጥንቃቄ ላይ ባመዘነበት ጨዋታ የቱኒዙ ክለብ የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በቻላሊ አማካኝነት ያመከነው እድል ተጠቃሽ ነው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ፈረሰኞቹ በሰላዲን ሰዒድ፣ አዳነ ግርማ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ እና ፕሪንስ ሰቨሪን ዋንጎ አማካኝነት ያገኙትን እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በሁለተኛው 45 የቻላሊ በሁለት ቢጫ ከሜዳ መወገዱን ተከትሎ ኤስፔራንሶች በ10 ተጫዋች ለመጫወት ተገደዋል፡፡ የምድቡ ሌላ ጨዋ ኪንሻሳ ላይ ቪታ ክለብ ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ይጫወታሉ፡፡ ኤስፔራንስ በአራት ነጥብ አንደኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡

 

ምድብ መ

ወደ ጋርኦ የተጓዘው አል አሃሊ ኮተን ስፖርት 2-0 መርታት ችሏል፡፡ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች አከታትሎ ያስቆጠራቸው ግቦች የካይሮውን ሃያል ክለብ ባለድል አድርገዋል፡፡ ናይጄሪያዊው ጁኒየር አጃዬ እና ሞሜን ዛካሪያ የድል ግቦቹን አስቆጠረዋል፡፡ አሃሊዎች በመልሶ ማጥቃት የተዳከመውን የኮተን ስፖርት የተከላካይ ክፍል የፈተሸ ቢሆንም በሰፊ ልዩነት ማሸነፍ የሚችልባቸው አድሎች አምክነዋል፡፡ አል አሃሊ ምድቡን በአራት ነጥብ ይመራል፡፡

ለ19ኛ ግዜ የሞሮኮ ቦቶላ ሊግ ክብርን ያገኘው ዋይዳድ ካዛብላንካ ከዛናኮ ጋር ዛሬ ይጫወታል፡፡

 

የማክሰኞ ውጤቶች

ክለብ ፌሮቫያሪዮ ዳ ቤይራ 0-0 አል ሂላል

ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ

ኮተን ስፖርት 0-2 አል አሃሊ

አል አሃሊ ትሪፖሊ 0-0 ዛማሌክ

ኤል ሜሪክ 1-2 ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል

 

የዛሬ ጨዋታዎች

09፡00 – ዛናኮ ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ

09፡00 – ካፕስ ዩናይትድ ከ ዩኤስኤም አልጀር

09፡30 – ኤኤስ ቪታ ክለብ ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *