የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ በድንገተኛ አደጋ ዛሬ ህይወቱ በአሳዛኝ ሁኔታ አልፏል፡፡ በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ መጀመሪያ በግብ ማስቆጠር ብቃቱ የተመሰከረለት አሰግድ በክለብ ደረጃ ለድሬዳዋ ኮካ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ተጫውቷል፡፡
አሰግድ የተወለደው በድሬዳዋ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ የተሳካ ግዜያትን ያሰለፈው በኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ አሰግድ ዛሬ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል፡፡ በ1990 ኢትዮጵያ ቡና የግቡፁን ሃያል አል አሃሊን በአፍሪካ የክለቦች ውድድር አሸንፎ ከውድድር ሲያስወጣ የቡናን ወሳኝ ግብ በማራኪ ሁኔታ ያስቆጠረው አመለ ሸጋው አሰግድ ነበር፡፡ አሰግድ በሲሸልሱ ሴንት ሚሼል ላይም አምስት ግቦችን በማስቆጠር በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ታሪክ መስራት የቻለ ድንቅ አጥቂ ነበር፡፡
አሰግድ ከእግርኳስ ጫማውን ከሰቀለ ወዲህ ፓሽን አካዳሚ የተባለ በታዳጊዎች እግርኳስ ላይ ለሚሰራ ቡድን በአሰልጣኝነት ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት በሆነው የአሰግድ ህልፈተ ዜና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ አስቀድሞም ለአሰግድ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ በቀድሞ የሃገራችን ድንቅ አጥቂ ህልፈት የተሰማትን ሃዘን እየገለፀች ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ እና ለኢትዮጵያ እግርኳስ ቤተሰብ መፅናናትን ትመኛለች፡፡