ኢትዮጵያ በ2019 በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ መክፈቻ ጨዋታ ከጋና ጋር ኩማሲ ላይ ላለባት ጨዋታ ዝግጅት ከጀመረች ከሁለት ሳምንታት በላይ ሆኗታል፡፡ ዋሊያዎቹ ዛሬ ጠዋት ወደ ኩማሲ በመዲናዋ አክራ በኩል ያቀኑ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም ለጨዋታው የሚጠቀሙባቸው 22 ተጫዋቾች ይዘው ወደ ስፍራው አቅንተዋል፡፡
በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እምብዛም አዲስ ያልሆኑ ፊቶች ቢታዩም የፋሲል ከተማውን አብድልራህማን ሙባረክ በስም ዝርዝሩ ውስጥ ሊካተት ችሏል፡፡ እንደ አብዱልራህማን ሁሉ የሀዋሳ ከተማው አማካይ ጋዲሳ መብራቴ በቡድኑ ውስጥ መካተት ችሏል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ሳላዲን ሰዒድ፣ አስቻለው ታመነ እና ሳላዲን በርጌቾ በሳምንቱ መጀመሪያ ቡድኑን ተቀላቅለው በስም ዝርዝሩ ውስጥ ሊካተቱ ችለዋል፡፡
አሜ መሃመድ፣ ተክለማሪያም ሻንቆ፣ አወት ገብረሚካኤል፣ ኤፍሬም አሻሞ እና አህመድ ረሺድ ለጋናው ጨዋታ በቡድኑ ውስጥ ሳይካተቱ ቀርተዋል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ ለሶከር ኢትዮጵያ እንዳስረዱት አምሰቱ ተጫዋቾች ቡድኑን ከጋና ጨዋታ በኃላ ተመልሰው እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል፡፡
ዋሊያዎቹ ረቡዕ ከሰዓት ከፋሲል ከተማ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገው በመጀመሪያው አጋማሽ ባሰቆጠሩት 3 ግቦች 3-0 አሸንፈዋል፡፡ ሳላዲን ሰዒድ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አብዱልራህማን ሙባረክ ቀሪዋን ግብ አክሏል፡፡
33 ልኡካንን የያዘው የአትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በፌድሬሽኑ የስራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ አበበ ገላጋይ እየተመራ ዛሬ ማለዳ ወደ አክራ አቅንቷል፡፡
ሙሉ ዝርዝር
ግብ ጠባቂዎች
አቤል ማሞ (መከላከያ)፣ ጀማል ጣሰው (ጅማ አባ ቡና)፣ ለአለም ብርሃኑ (ሲዳማ ቡና)
ተከላካዮች
አዲስ ተስፋዬ (መከላከያ)፣ አስቻለው ታመነ፣ ሳላዲን በርጌቾ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ አብዱልከሪም መሃመድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ሲዳማ ቡና)፣ ሙጂብ ቃሲም፣ ተስፋዬ በቀለ (አዳማ ከተማ)፣ ስዩም ተስፋዬ (ደደቢት)
አማካዮች
ሽመልስ በቀለ (ፔትሮጀት/ግብፅ)፣ ጋቶች ፓኖም (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ብሩክ ቃልቦሬ (አዳማ ከተማ)፣ ሽመክት ጉግሳ (ደደቢት)፣ ሙሉአለም መስፍን (ሲዳማ ቡና)፣ ጋዲሳ መብራቴ (ሃዋሳ ከተማ)
አጥቂዎች
ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)፣ ኡመድ ኡኩሪ (ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ/ግብፅ)፣ አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አብዱልራህማን ሙባረክ (ፋሲል ከተማ)፣ ሳላዲን ሰዒድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)