አራት አሰልጣኞች ለስልጠና ወደ አሜሪካ ያመራሉ

“ላ ሊጋ ሜተዶሎጂ” በሚል መጠርያ በስፔናውያን አሰልጣኞች አማካኝነት በዩናይትድ ስቴትስ የሚዘጋጅ የአሰልጣኞች ስለልጠና ላይ ለመካፈል 4 ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች ከቀናት በኋላ ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ታውቋል፡፡

በዘንድሮ አመት ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀን በሚቆየው ስልጠና ውበቱ አባተ (ሀዋሳ ከተማ) ፣ አስራት አባተ (አዲስ አበባ ከተማ) ፣ ብርሃኑ ባዩ ( ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ ብርሃኑ ግዛው (ኢትዮዽያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን) ደረጃ ሁለትን ስልጠና የሚወስዱ ይሆናል። ስልጠናውን በአግባቡ ተከታትለው የሚያጠናቅቁ ከሆነም በቀጣይ አመት ወደ ባርሴሎና ከተማ በማምራት በታላቁ የላ ማሲያ ማዕከል ስልጠና የደረጃ ሶስት ስልጠና ይወስዳሉ፡፡

ባለፉት አመታት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሰልጣኞች ስልጠናውን የወሰዱ ሲሆን ባሳለፍነው አመት ኢትዮጵያውያን አሰልጣኞች የደረጃ አንድ ስልጠና ወስደው መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

ኢትዮዽያውያን አሰልጣኞች ይህን የስልጠና ዕድል እንዲያገኙ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማመቻቸት ትልቁን አስተዋፆኦ ያደረገው በአሜሪካ የሚኖረው አምሳሉ ፋንታሁን የተባለ ኢትዮዽያዊ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *