ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ የክለቦች እግርኳስ ውድድር አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል

በ2017ቱ የቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ውድድር በመሳተፍ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ የኮንጎውን ኤ ኤስ ቪታ በአዲስ አበባ ስታዲየም አስተናግዶ በሳላህዲን ሰዒድ የ60ኛ ደቂቃ ግብ 1 – 0 ካሸነፈ በኋላ በውድድሩ ታሪክ በ7 ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ የመጀመሪያው ክለብ በመሆን አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል።

የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እ.ኤ.አ. በ1997 በአዲስ መልክ ከተጀመረ በኋላ ዘንድሮ ለ21ኛ ጊዜ እየተደረገ ሲሆን በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያለማስተናገድ ሪከርዱም በግብፁ ሃያል ክለብ ዛማሌክ የተያዘ ነበር። በ2014ቱ ውድድር ዛማሌክ በቅድመ ማጣሪያው የኒጀሩ ኤኤስ ዱዋኔስ ኒያሜይን 2-0 እና 1-0፣ በመጀመሪያው ዙር የአንጎላው ካቡስኮርፕን 0-0 እና 1-0፣ እንዲሁም በሁለተኛው ዙር የዛምቢያውን ንካና 0-0 እና 5-0 በማሸነፍ በድምር ውጤት የምድብ ውድድሩን በተቀላቀለበት የ6 ጨዋታ የማጣሪያ ጉዞ ግብ ሳይቆጠርበት በመዝለቅ ያስመዘገበው ሪከርድ ዘንድሮ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሻሽሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2017ቱ የቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ የሲሼልሱን ኮት ድ ኦር በድምር ውጤት 5-0 (0-2 እና 3-0)፣ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ የኮንጎ ብራዛቪሉን ኤሲ ሊዮፓርድስ በአጠቃላይ 3-0 (0-1 እና 2-0) ሲያሸንፍ በምድብ ውድድሩ የመጀመሪያ 3 ጨዋታዎች ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ኤስፔራንስ ደ ቱኒስ ጋር 0-0 ተለያይቶ የኮንጎውን ኤ ኤስ ቪታ ደግሞ 1-0 አሸንፏል። በእነዚህ 7 ጨዋታዎች ላይ መረባቸውን ያላስደፈሩት ፈረሰኞቹ እና በተመሳሳይ ዘንድሮ (በ5 ጨዋታዎች) ግብ ያላስተናገደው የግብፁ ክለብ አል አህሊ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ባለቤት መሆናቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ።

ዪጋንዳዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያላስተናገደ ግብ ጠባቂ ሪከርድን ከዛማሌኩ አብደልዋሂድ ኤል ሳይድ መረከብ የሚችልበት ዕድል የነበረው ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤስፔራንስን ጋር ባደረገው የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ባጋጠመው የጉልበት ጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ አጋጣሚውን እንዲያጣ አድርጎታል።

ፈረሰኞቹ ዘንድሮ እያሳዩ በሚገኙት አስደናቂ ግስጋሴ በመቀጠል የምድብ ጨዋታዎችን በሙሉ ሳይሸነፉ የሚያጠናቅቁ ከሆነም ከዚህ በፊት 8 ክለቦች ብቻ የደረሱበትን ስኬት ማስመዝገብ ይችላሉ። የጋናው ኸርትስ ኦፍ ኦክ፣ የቱኒዚያዎቹ ኤስፔራንስ እና ኤቱዋል ደ ሳህል፣ የግበፁ አል አህሊ፣ የኮትዲቯሩ ኤኤስኢሲ ሚሞሳስ፣ የናይጄሪያው ኢንያምባ እና የአልጄሪያዎቹ ኢ ኤስ ሴቲፍ እና ጄኤስ ካቢልዬ በውድድሩ ታሪክ ምድባቸውን ሳይሸነፉ ማጠናቀቅ የቻሉ ብቸኛ ክለቦች ናቸው።

የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቀጣይ ጨዋታዎች ሰኔ 13 እና 14 ሲደረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ኪንሻሳ በመጓዝ የኮንጎውን ኤኤስ ቪታ የሚገጥም ይሆናል። በሌላው የምድቡ ጨዋታም መሪው ኤስፔራንስ ከአምናው ሻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር በቱኒስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *