የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አግቢነትን በ14 ግቦች እየመራ የሚገኘው ኡመድ ኡኩሪ እሁድ ለህትመት ከበቃው የቅዱስ ጊዮርጊስ ልሳን ‹‹ ልሳነ-ጊዮርጊስ ›› ጋዜጣ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጓል፡፡ ኡመድ ከጋዜጣው ጋር ያደረገውን ቆይታ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታታዮች በሚመች መልኩ እንዲህ አሰናድተነዋል፡፡
ኡመድ ኡኩሪ መከላከያን ለቆ በ2 አመታት ኮንትራት ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ባለፈው የውድድር ዘመን መጀመርያ ነበር፡፡ አምና ቡድኑ በጀርመናዊው አሰልጣኝ ሚኬል ክሩገር እየተመራ በአፍሪካ ውድድሮች ላይ አንፃራዊ መልካም ውጤቶችን ሲያስመዘግብ ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠርላቸው የነበረውም ኡመድ ነበር፡፡ አጥቂው በአሰልጣኙ አመራር በተለይም በአፍሪካ ውድድር ላይ ስኬታማ ጊዜ ቢያሳልፍም የአሰልጣኙ አጨዋወት ምቾት እንዳልሰጠው ይናገራል፡፡
‹‹ አሰልጣኛችን (ክሩገር) አፈግፍገን እንድንከላከልና በፍጥነት የመልሶ ማጥቃት እንድንፈፅም ያዘን ነበር፡፡ ይህ አጨዋወት ለኔ እና ለሌሎች አጥቂዎች ምቾት አልሰጠንም ነበር፡፡ ››
‹‹ ዘንድሮ አሰልጣኞቻችን ነፃነት ሰጥተውናል፡፡ የማጥቃት አጨዋወትን ይዘው መጥተዋል፡፡ ብዙ የግብ እድሎችን እንድንፈጥርም ይፈልጋሉ፡፡›› ሲልም ዘንድሮ በሁለት ሆላንዳዊያን ( ማርት ኑይ እና ሬኔ ፌለር ) የተመራው ቅዱስ ጊዮርጊስን ከአምናው ጋር ያነፀፅራል፡፡
ከጋምቤላ አኝዋክ ብሄረሰብ የተገኘው ኡመድ መጠርያ ስሙን ያገኘው በአኝዋክ ብሄረሰብ ባህል መሰረት ነው፡፡ በብሄረሰቡ የመጀመርያ ልጅ ሲወለድ ኡመድ የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ የ‹‹በኩር›› ልጅ የሆነው ኡመድ የዘንድሮው የሊግ ዋንጫም በእግርኳስ ህይወቱ የ‹‹በኩር›› ድሉ ነው፡፡ ‹‹ ከዚህ በፊት ከመከላከያ ጋር 3ኛ ፤አምና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 2ኛ ደረጃ ያገኘሁ ቢሆንም የዋንጫ ድልን አጣጥሜው አላውቅም፡፡ ዘንድሮ በማሳካቴ ተደስቻለሁ፡፡ ››
ኡመድ የመጀመርያ ድሉ ደስተኛ ቢያደርገውም ያን ያህል ጮቤ ያስረገጠው አይመስልም ‹‹ ፕሪሚየር ሊጉን ማሸነፋችን ደስታን ፈጥሮልኛል፡፡ ነገር ግን ድሉን የጠበቅኩት በመሆኑ ከልክ ያለፈ ደስታ አልተሰማኝም፡፡ እኔና የቡድን ጓደኞቼ የውድድር ዘመኑ ሳይጋመስ በፊት ዋንጫውን እንዳነሳነው ይሰማን ነበር፡፡ እስከ መጨረሻው የሚታገለን ቡድን ቢኖርና በመጨረሻው ጨዋታ ቻምፒዮንነታችንን ብናረጋግጥ ይበልጥ ደስተኛ እሆን ነበር፡፡›› ሲል የፉክክር አለመመጣጠኑ በሱ እና የቡድን ጓደኞቹ ላይ መቀዛቀዝ እንደፈጠረ ያስረዳል፡፡
ባለፉት 2 የውድድር ዘመናት እንደ ኡመድ ስሙ ከበርካታ የአፍሪካ ክለቦች ዝውውር ጋር የተያያዘ ተጫዋች ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ከጭምጭምታ እስከ ተረጋገጠ የድርድር ሂደት ኡመድ ከበርካታ ክለቦች ጋር ተያይዞ ከርሟል፡፡ በመጨረሻ የተሳካው ግን ከ1 ወር በፊት ነው፡፡ ኡመድ ስላልተሳኩት እና ስለ ኢትሃድ አሌሳንድርያ ዝውውሩ ይናገራል፡፡
‹‹ የዝውውር ጥያቄዎች ይመጡ የነበረው መከላከያ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡ ከክለብህ ጋር ውል እያለህ ስለ ዝውውር ማውራት በኛ ሃገር አለመለመዱ ለዝውውሮች አለመሳካት ትልቅ ተፅእኖ ፈጥሮብኛል፡፡ ከደቡብ አፍሪካው ጆሞ ኮስሞስ ጋር ከስምምነት ላይ ደርሰን በቪዛ ችግር ምክንያት ሳይሳካ ቀረ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከገባሁ በኋላም ከዛማሌክ ጋር ተነጋግረን ነበር፡፡ እሱም ሳይሳካ ቀረ፡፡ በሊቢያም እንዲሁ ..››
‹‹ ከሊቢያ የመጣው እድል ያመለጠኝ ወኪሌ ከእኔ ዝውውር ከፍተኛ ገንዘብ ለማግኘት ፈልጎ ይመስለኛል፡፡ የዛማሌክ የፋይናንስ ችግር ደግሞ ወደ ካይሮው ክለብ እንዳልዘዋወር ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ኢ ኤን ፒ ፒ አይም እኔን ማዘዋወር የፈለገው ቡድኑ ዘንድሮ ወደ ሁለተኛው ዲቪዝዮን ካልወረደ እንደሆነ አሰልጣኙ ሚኬል ክሩገር ነግሮኛል፡፡ በመሃል ከአሌሳንድሪያዎች ጋር ተስማማሁ፡፡ ››
‹‹ አዲሱ ክለቤ ከግብፅ ታላላቅ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ ለ3 አመት የፈረምኩ ሲሆን የኮንትራቱ አጠቃላይ ዋጋ 5 መቶ ሺህ ዶላር ነው፡፡ አሁን የሁለቱን አመት 3 መቶ ሺህ ዶላር ተቀብያለሁ፡፡ ከፊርማ ክፍያው በተጨማሪ ሌሎች ጥቅማጥቅሞች አሉት፡፡ ቤት ፣ መኪና እና በአመት 2 ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለማደርገው ጉዞ የአውሮፕላን ትኬት ለእኔ እና ባለቤቴ ይቀርብልናል፡፡ ››
በእግርኳስ ከማትታወቅ መንደር ተነስቶ የሃገሪቱን ትልቅ ክለብ በፊት አውራሪነት እስከመምራት የደረሰው ኡመድ በባህር ማዶም ህልሙን መኖር እንደሚቀጥል ተስፋ ያደርጋል፡፡
‹‹ ከኢትሃድ አሌሳንድሪያ ጋር ስፈራረም ፣ ማልያውን ይዤ እና የህክምና ምርመራዬን ጭምር የሚያሳዩ ምስሎች በክለቡ ድረ-ገፅ ሲለቀቁ ማየቴ አስገርሞኛል፡፡ ተጫዋቾች ይህንን ሲያደርጉ የምመለከተው በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ነበር፡፡
‹‹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ኮንትራቴን ጨርሼ ወደ አሌሳንድሪያ ሳመራ ክለቡ የሚያቀርብልኝን መኪና እመርጣለሁ፡፡ በክለቡ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች የሚጠቀሙት ቼቭሮሌት መኪና ነው፡፡ እዚህ ባለስልጣናት እና ባለሃብቶች ላይ የማየውን መኪና ልጠቀም እችላለሁ፡፡ ››
በመጨረሻም አዚህ ለደረሰበት ደረጃ ያበቁትን ቤተሰቦቹን ፣ ባለቤቱን ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ አመራሮችን እና ደጋፊዎችን ያመሰግናል፡፡