ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ለ ፉክክር አሁንም ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ 29ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ተካሂደው ወደ ፕሪምየር ሊግ የመግባት ተስፋ ያላቸው ቡድኖች በሙሉ አሸንፈው የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ እጅግ ተጠባቂ እንዲሆን አድርገውታል፡፡

ወደ አርሲ ነገሌ ያመራው መሪው ጅማ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ መመለስ ችሏል፡፡ ግብ ባልተስናገደበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በሊጉ የመቆየት ጭላንጭል ተስፋ ይዞ ወደ ሜዳ የገባው አርሲ ነገሌ የግብ ሙከራ ያደረገ ሲሆን የጥንቃቄ ጨዋታ የመረጡት ጅማዎችም መልካም የግብ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር፡፡ ከዕረፍት መልስ ተጭነው የተጫወቱት ጅማ ከተማዎች በ70ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂው አቅሌስያስ ግርማ ባስቆጠራት ግብ 1-0 በማሸነፍ ውድ 3 ነጥብ ይዘው ተመልሰዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ አርሲ ነገሌ የ’ምድብ ሀ’ዎቹ አራዳ ክፍለከተማ እና ሰሜንሸዋ ደብረብርሀን ተከትሎ ወደ አንደኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል፡፡

ወደ ነቀምት የተጓዘው ተከታዩ ሀድያ ሆሳዕና በተመሰሳይ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ለመጫወት እጅግ አስቸጋሪ በነበረ ሜዳ ላይ በተደረገው ጨዋታ የቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ ሳምሶን ቆልቻ በ33ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ጎል ሀድያን ለ 1-0 ድል አብቅታለች፡፡

ወልቂጤ ላይ በበርካታ ደጋፊ እና አስደናቂ ድጋፍ ታጅቦ ደቡብ ፖሊስን የገጠመው ወልቂጤ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት በሚደሰገው ፉክክር ወስጥ መቆየት ችሏል፡፡

በመጀመሪያው አሰራ አምስት ደቂቃ ተጭነው የተጫወቱት ወልቂጤዎች በ3ኛው ደቂቃ በአክሊሉ ተፈሪ አማካኝነት የጨዋታዋን ብቸኛ ግብ ማግኘት ችለዋል፡፡

ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ ፉክክር የተስተዋለ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጎል እድሎች ተፈጥረው ነበር፡፡ በደቡብ ፖሊስ በኩል ሀብታሙ ገዛህኝ እና ብርሃኑ በቀለ ፤ በወልቂጤ በኩል ተቀይረው የገቡት ብሩክ በየነ ፣ ሚካኤል ወልደሩፋኤል እና እስራኤል መንግስቴ የሞከሯቸው ኳሶች በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

ሀላባ ላይ ፌዴራል ፖሊስን የገጠመው ሀላባ ከተማ በግብ ተንበሻብሾ ወጥቷል፡፡ በ18 ደቂቃ ስንታየው መንግስቱ ቀዳሚዋን ጎል ሲያስቆጥር በ28ኛው ደቂቃ በፌዴራል የግብ ክልል ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ዘካርያስ ፍቅሬ ወደ ጎልነት ቀይሮታል፡፡ በ58ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ፍቅሬ ለራሱ ሁለተኛውን ለቡድኑ ደግሞ ሦስተኛውን ግብ ሲያስቆጥር አምበሉ ትዕግስቸቱ አበራ በ60ኛው ደቂቃ ማሳረግያዋን ግብ አስቆጥሯል፡፡

ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ዲላ ከተማን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ለሻሸመኔ ከተማ በ60ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ቶማስ እና በ73ኛው ደቂቃ ላይ አቡድላዚዝ ዑመር የድል ጎሎቹን ማስቆጠር ችለዋል፡፡

በሌሎች የምድብ ለ ጨዋታዎች ከፋ ቡና ጅንካን ከተማን በኡጁሉ አቤሎ የ40ኛ ደቂቃ ጎል 1-0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ፖሊስ ነገሌ ቦረናን አስተናግዶ  በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ስልጤ ወራቤ ከ ናሽናል ሲሚንት ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለ ጎል የተጠናቀቀ የሳምንቱ ብቸኛ መርሀግብር ነው፡፡

ተጠባቂው የመጨረሻ ሳምንት

አሁን ላይ ሆነን የደረጃ ሰንጠረዡን ስንመለከት 4 ቡድኖች ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመግባት ተስፋ አላቸው ጅማ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ተመሳሳይ 53 ነጥቦች ሲሰበስቡ ወልቂጤ ከተማ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተላል፡፡ 47 ነጥብ የሰበሰበው ሀላባ ከተማም ጂንካ ከተማን 2-1 እየመራ ከተቋረጠው ጨዋታ 3 ነጥብ ካገኘ በ50 ነጥቦች በፉክክሩ ውስጥ መቆየት ይችላል፡፡ እጅግ አጓጊ የሚያደርገው ደግሞ በ30ኛው ሳምንት አራቱ ቡድኖች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እርስ በእርስ መሆናቸው ነው፡፡ ጅማ ላይ ጅማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ ፣ ሆሳዕና ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከ ሀላባ ከተማ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ወደ ፕሪምየር ሊጉ የማለፍ እጣፈንታቸው ይለያል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *