የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ዛሬ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች መካሄድ ሲጀምሩ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ኤኤስ ቪታ ክለብን ይገጥማል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድብ ሶስት የቱኒዚያውን ኤስፔራንስን ተከትሎ በ5 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ኪንሻሳ ላይ ከቪታ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለማለፍ የተሻለ እድል ይኖረዋል፡፡ ፈረሰኞቹ ከሁለት ሳምንት በፊት አዲስ አበባ ላይ ቪታን በሳላዲን ሰዒድ የሁለተኛ አጋማሽ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ቪታ በዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በምድብ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች የተሸነፈ ሲሆን የተከላካይ መስመሩ ጫና ሲበዛበት በቀላሉ ግብ ሲቆጠርበት ተስተውሏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅጣት ያጣውን አዳነ ግርማን መልሶ ሲያገኝ ቪታ ክለብ የግራ መስመር ተከላካዩን ጆይስ ሎማሊሳን መልሶ የማግኘት እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ጫና የበረታባቸው የቪታው አሰልጣኝ ፎሎሮ ኢቤንጌም በቡድኑ ያላቸው ቆይታ ወደ ማለቁ እየተቃረበ ይመስላል፡፡ ቪታ ክለብ ከጨዋታው ነጥብ የማያገኝ ከሆነ ከቻምፒየንስ ሊጉ መሰናበቱን የሚያረጋግጥ የመጀመሪያው ክለብ ይሆናል፡፡ ጨዋታውን ዛምቢያዊው ጃኒ ሲካዝዌ በዋና ዳኛነት ሲመሩ ረዳቶቻቸው ጄርሰን ኢሚሊያኖ ዶ ሳንቶስ ከአንጎላ እና አሞስ ቻልዌ ከዛምቢያ ናቸው፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ አብዛኞቹን ቋሚ ተሰላፊዎቹን ባላሰለፈበት ጨዋታ ከፕሪምየር ሊጉ የወረደውን አዲስ አበባ ከተማን 3-0 ሲያሸንፍ በሊና ፉት ውድድር ቻምፒዮን ለመሆን ከሃያሉ ቲፒ ማዜምቤ እና ዲሲ ሞቱማ ፔምቤ ጋር እየተፋለመ ይገኛል፡፡ ሶስት ጨዋታዎች በሚቀሩት የሊና ፉት ሊግ ቪታ ክለብ ባሳለፍነው አርብ ቡካቩ ዳዋን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኪንሻሳ በሚገኘው ስታደ ደ ማርቲርስ የሚደረገውን ጨዋታ በቤን ስፖርትስ 2 የቀጥታ ስርጭት ሽፋንን ያገኛል፡፡
በምድብ አራት ካዛብላንካ ላይ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ ዋይዳድ ካዛብላንካ አል አሃሊን ያስተናግዳል፡፡ አል አሃሊ በሜዳው ዋይዳድን 2-0 ያሸነፈ ሲሆን ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ከድል ለራቀው ዋይዳድ ጨዋታው ወሳኝ ነው፡፡ አሰልጣኝ ሁሴን አሞታ ዋይዳድን ከቦቶላ ሊግ ክብር ቢያበቁም በቻምፒየን ሊግ ወጥ የሆነ አቋም ቡድናቸው ማሳየት ተስኖታል፡፡ በአንፃሩ አል አሃሊ የግብፅ ፕሪምየር ሊግን ያለተቀናቃኝ ያሸነፈ ሲሆን በአሰልጣኝ ሆስኒ ኤል ባድሪ እየተመራም ከምድቡ ለማለፍ የሚያስችለውን ነጥብ ለማስመዝገብ ተቃርቧል፡፡ ምድቡን አል አሃሊ አና የዛምቢያው ዛናኮ በ7 ነጥብ ሲመሩት ዋይዳድ በ4 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶስተኛ ነው፡፡
ኦምዱሩማን ላይ የውጤት ቀውስ ውስጥ የገባው ኤል ሜሪክ የሞዛምቢኩን ፎሮቫያሪዩ ደ ቤይራን ይገጥማል፡፡ ኤል ሜሪክ ማፑቶ ላይ በፎሮቫያሪዮ ያልተጠበቀ ሽንፈትን የቀመሰ ሲሆን በምድብ 1 በአንድ ነጥብ ብቻ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡ ፎሮቫያሪዮ በ4 ነጥብ ሁለተኛ ሲሆን ኦምዱሩማን ላይ ነጥብ ማስመዝገብ ከቻለ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስችለዋል፡፡ የሜሪኩ አሰልጣኝ ዲዬጎ ጋርዚያቶ ቡድናቸው በጨዋታው ከማሸነፍ ውጪ እንዲያሳካ አይፈልጉም፡፡
የዛሬ ጨዋታዎች
15፡00 – ኤኤስ ቪታ ክለብ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (11፡00 ሰዓት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር) (ኮምፕሌክስ ኦምኒስፖርትስ ስታደ ደ ማርቲርስ)
23፡00 – ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ ከ አል አሃሊ (ኮምፕሌክስ መሃመድ 5ተኛ)
23፡00 – ኤል ሜሪክ ከ ክለብ ፌሮቫሪዮ ደ ቤይራ (ኤል ሜሪክ ስታዲየም)