ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ፡ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ

የካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ አፍሪካ ከተሞች ይደረጋሉ፡፡ ሰባት ጨዋታዎች ዛሬ የሚካሄዱ ሲሆን ክለቦቹ ያላቸው የነጥብ መቀራረብን ተከትሎ የሚደረጉት ጨዋታዎች በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡

ምድብ 1

የዩጋንዳው ኬሲሲኤ ፖርት ሃርኮት ላይ ሪቨርስ ዩናይትድን ይገጥማል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት የዩጋንዳ ዋንጫ በማሸነፍ የሁለትዮሽ ዋንጫ ባለቤት መሆኑን ያረጋገጠው የካምፓላው ክለብ በኮንፌድሬሽን ዋንጫው አስገራሚ ግስጋሴ ላይ ይገኛል፡፡ ሁለት ጨዋታዎችን የተሸነፈው የናይጄሪያው ሪቨርስ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ሲከብደው አይስተዋልም፡፡ ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ጨዋታ ኬሲሲኤ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በሰሜን አፍሪካ ደርቢ የምድቡ መሪ ፉስ ራባት ቱኒዝ ላይ ክለብ አፍሪካን ይፋለማል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ በሞሮኮ መዲና ድል የቀናው ፉስ ቱኒዚያ ላይ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል፡፡ ክለብ አፍሪካ ቅዳሜ እለት የቱኒዚያ ዋንጫ ቻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጉዞውን ለማስተካከል ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡

ምድብ 2

ዛሬ አንድ ጨዋታ አልጀርስ ላይ ሲካሄድ ኤምሲ አልጀር ምባባኔ ስዋሎስን ይገጥማል፡፡ በአልጄሪያ ሊግ ሞቢሊስ ቻምፒዮኑን ሴቲፍን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቅቋል፡፡ በአልጄሪያ ከፍተኛ ተከታይ ያለው ክለብ የሆነው ኤምሲ አልጀር ከዓመት ዓመት መሻሻልን እያሳየ ሲሆን በ2018 ከወዲሁ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ የስዋዚላንዱ ክለብ ምባባኔ ስዋሎስ በዘንድሮ አፍሪካ ክለቦች ውድድር ክስተት የሆነ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ከተጋጣሚው ኤምሲ አልጀር ያለው የነጥብ ልዩነት አንድ ብቻ መሆኑ ጨዋታው ትኩረትን እንዲገኝ አስችሏል፡፡

ምድብ 3

የአንጎላው ሬክሬቲቮ ዱ ሊቦሎ ዜስኮ ዩናይትድን እንዲሁም አል ሂላል ኦባያድ ስሞሃን የሚያስተናግዱበት ጨዋታ ዛሬ ይደረጋል፡፡ የምድቡ መሪ ዜስኮ ዩናይትድ ወደ ሩብ ፍፀሜ የሚያደርገውን ጉዞ የተሳካ ለማድረግ ሊቦሎን ማሸነፍ ይጠብቅበታል፡፡ ሁለት ጨዋታዎች ተሸንፎ አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ የቻለው ሊቦሎ በሜዳው የሚያሳየውን ጥንካሬ ተከትሎ የአምና የቻምፒየንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ሊቸገር እንሚችል ይጠበቃል፡፡

ኦባያድ ላይ ለመጀመሪያ ግዜ በኮንፌድሬሽን ዋንጫው እየተሳተፈ የሚገኘው አል ሂላል ኦባያድ የግብፁን ስሞሃን ይገጥማል፡፡ ስሞሃ በምድቡ ከኦባያድ ጋር በእኩል 4 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሁለተኛ እና ሶስተኛ ነው፡፡ ኦባያድ በሜዳው ጠንካራ ሲሆን ስሞሃ ከሜዳው ውጪ በዜስኮ ዩናይትድ ተሸንፏል፡፡

ምድብ 4

ሶስት ክለቦች በእኩል 5 ነጥብ ተያይዘው ባሉበት ምድብ የወቅቱ ቻምፒዮን ቲፒ ማዜምቤ ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቶ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ሲገጥም የጊኒው ሆሮያ ሶስት ጨዋታዎች የተሸነፈውን የጋቦኑን ሞናናን ያስተናግዳል፡፡ ማዜምቤ ሉቡምባሺ ላይ ከሱፐርስፖርት ጋር 2 አቻ የተለያየ ሲሆን ሱፐርስፖርት ያለው የግብ ማስቆጠር ሪከርድ የተሻለ መሆኑ ለሃያሉ ኮንጎ ክለብ ጨዋታውን ፈታኝ እንደሚያደርግበት ይጠበቃል፡፡ የደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆናቸውን ተከትሎ ሱፐርስፖርትን ስኮትላናዳዊው ስትዋርት ባክተር የተለያየ ሲሆን በግዜያዊ አሰልጣኝ እየተመራ ለጨዋታው ይቀርባል፡፡ ሱፐርስፖርት በሶስት ጨዋታዎች 9 ግቦች በማስቆጠር የፊት መስመሩ ጥንካሬን ያስመሰከረ ሲሆን ተከላካይ መስመሩ በአንፃሩ 7 ግቦችን አስተናግዷል፡፡

ኮናክሬ ላይ ሆሮያ ጨዋታዎችን ማሸነፍ የከበደውን ሞናናን ይገጥማል፡፡ በጨዋታው የማሸነፍ ቅድመ ግምትን የወሰደው በምድቡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሆሮያ ነው፡፡ ሆሮያ ጨዋታው ካሸነፈ ደረጃውን የሚያሻሽል ይሆናል፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

15፡00 – ክለብ ሬክሬቲቮ ዶስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ ከ ዜስኮ ዩናይትድ (ኢስታዲዮ ደ ካሉሉ)

16፡00 – ሪቨርስ ዩናይትድ ከ ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ (ሊብሬሽን ስታዲየም)

16፡00 – ሆሮያ አትሌቲክ ክለብ ከ ሲኤፍ ሞናና (ስታደ ሴፕቴምበር 28)

19፡00 – ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ከ ቲፒ ማዜምቤ (ሊካስ ማስተርፒስስ ሞሪፔ ስታዲየም)

22፡00 – ክለብ አፍሪካ ከ ፋት ዩኒየን ስፖርት (ስታደ ኦሎምፒክ ራደስ)

23፡00 – አል ሂላል አባያድ ከ ስሞሃ (አል ኦባያድ ስታዲየም)

23፡00 – ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር ከ ምባባኔ ስዋሎስ (ስታደ ጁላይ 5 1962)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *