የደደቢት ተጨዋቾች ከክለቡ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በቅርብ አመታት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት እና ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን አቅሙን እያሳየ የሚገኘው ደደቢት እግር ኳስ ክለብ በዘንድሮ አመት የውድድር ዘመን ለተጨዋቾቹ ደሞዝ ለመክፈል ሲቸገር ተስተውሏል፡፡

በዚህም ምክንያት ክለቡ የአምስት ወር ደሞዝ አልከፈለንም በማለት የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች የሆኑት አይናለም ኃይሌ ፣ አስራት መገርሳ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አክሊሉ አየነው እና ዳዊት ፍቃዱ ልምምድ ካቋረጡ 15 ቀናትን ማስቆጠራቸው ታውቋል፡፡ ልምምድ የማቋረጣቸው ምክንያት በተደጋጋሚ በስልክም ሆነ በአካል ቢሮ ድረስ በመሄድ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ካለማግኘታቸው በተጨማሪ ሌሎች የቡድኑ አባላት የደሞዝ ክፍያ ሲፈፀምላቸው ለእነሱ አለመከፈሉ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ተጫዋቾቹም ቅሬታቸውን ለክለቡ እንዲሁም በግልባጭ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብተዋል።

ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው አካላት ለማወቅ እንደቻልነው ክለቡ ላስገቡት የደሞዝ ጥያቄ የተሰጣቸው ደብዳቤ የክለቡን ተጨዋቾች በማሳደም ለፈፀሙት ተግባር አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድ የሚያሳውቅ መሆኑ ታውቋለል፡፡

ከአምስቱ ተጫዋቾች መካከል ዘንድሮ ቡድኑን ከተቀላቀለው አስራት መገርሳ በስተቀር አራቱ ተጨዋቾች በዘንድሮ አመት ከደደቢት ጋር ያላቸው ኮንትራት የሚፈፀም ይሆናል።

ደደቢት እግርኳስ ክለብ አስራ አንድ የሚሆኑ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ የሚያደርጉለት ቢሆንም በዘንድሮ የውድድር አመት ክፉኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠማቸው በተለያየ ወቅት የክለቡ አመራሮች መግለፃቸው ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ከ17 እና 20 አመት በታች ቡድኑ ክልል ላይ ወጥቶ መጫወት ሲገባው ከአቅም እጥረት ጋር በተያያዘ ፎርፌ መሰጠቱ የሚታወስ ሲሆን በዘንድሮ አመት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የምድቡን እና የማጠቃልያው ውድድር አሸናፊ የሆነው የሴቶች ቡድኑም ለወራት ደሞዛቸው ሳይከፈላቸው መቅረቱን ክለቡም አምኖ በቅርቡ ክፍያ እንደሚፈጽም መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንትም ለሴቶች ቡድኑ አባላት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ክፍያ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *