የቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አራተኛ ጨዋታዎች ዕረቡ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ተጠናቅቀዋል፡፡ በኢትዮጵያው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚገኝበት ምድብ የተጫወቱት ኤስፔራንስ እና የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ያለግብ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቅቀዋል፡፡
ምድብ 1
አል ሂላል ኦምዱሩማን ላይ ኤትዋል ደ ሳህልን አስተናግዶ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ አቻ ሊወጣ ችሏል፡፡ በጨዋታው ሁለቱም ክለቦች የግብ እድሎች የፈጠሩ ሲሆን በተለይ ባለሜዳዎቹ ሂላሎች በተደጋጋሚ ያገኟቸውን ወርቃማ እድሎች መጠቀም አለመቻላቸው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው እንዳይወጡ አግዷቸዋል፡፡ በጨዋታው ላይ የሂላሎቹ አውገስቲን ኦክራ አና በሽር ቢሻ በተደጋጋሚ ግብ ሊሆኑ የሚችሉ እድሎችን አምክነዋል፡፡ ራሚ ቤዳዊ ሂላል ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው ማራቅ ያልቻሉትን የማዕዘን ምት ከመረብ አዋህዶ ኤትዋልን በ86ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሲያደርግ ሱዳናዊው ኢንተርናሽናል ቢሻ በ91ኛው ሳሊዮ ኦታራ ያሻገረውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል፡፡ ምድቡን አሁንም ኤትዋል ደ ሳህል በ8 ነጥብ ሲመራ አራት ጨዋታ አቻ የወጣው አል ሂላል የከተማ ተቀናቃኙን ኤል ሜሪክን በግብ ክፍያ በልጦ ሁለተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል፡፡ በዚህ ምድብ አል ሂላል፣ ኤል ሜሪክ እና ፌሮቫያሪዮ ቤይራ እኩል አራት ነጥብ ያላቸው መሆኑ ቀሪ ሁለት ጨዋታዎች በጉጉት እንዲጠበቁ አድርጓል፡፡
ምድብ 2
አል አሃሊ ትሪፖሊ እና ዩኤስኤም አልጀር ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል፡፡ በገለልተኛ ሜዳ ቱኒዚያ ሴፋክ ላይ ካፕስ ዩናይትድን የገጠመው አል አሃሊ ትሪፖሊ 4-2 አሸንፏል፡፡ ሃራሬ ላይ በተመሳሳይ ውጤት ማሸነፍ የቻለው የሊቢያው መዲና ክለብ በሁለት ጨዋታዎች 8 ግቦችን ካፕስ ዩናይትድ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ሳላ ጣሂር አሃሊ ትሪፖሊን ቀዳሚ ሲያደርግ ሮናልድ ፕፉምቢድዛይ እና ሮናልድ ቺትዮ ያስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ካፕስን የመጀመሪያውን 45 በመሪነት እንዲጠናቀቅ አስችለዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ሳላ ጣሂር ቡድኑን አቻ ሲያደርግ መሃመድ አል ጋኖዲ እና ሞኤድ ኤላፊ ያስቆጠሯቸውን ተጨማሪ ግቦች አል አሃሊ ትሪፖሊን ለድል አብቅተዋል፡፡ ሞኤድ ኤላፊ በቻምፒየንስ ሊግ ያስቆጠረውን የግብ መጠን ወደ 6 ማድረስ ችሏል፡፡
አልጀርስ ላይ የአልጄሪያ ሊግ ሞቢሊስ ክብሩን ለኢኤስ ሴቲፍ አሳልፎ የሰጠው ዩኤስኤም አልጀር ዛማሌክን 2-0 አሸንፏል፡፡ ብርቱ ፉክክር በታየበት የሰሜን አፍሪካ ደርቢ ጨዋታ ብዙ የግብ እድሎች ተፈጥረዋል፡፡ ሬዳ ቤላሰን ዩኤስኤምን ቀዳሚ የሆነበትን ግብ በ44ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ ዛማሌክ ወደ ጨዋታ ሊመልስበት የሚችልበትን እድል አማካዩ ሺካባላ አግኝቶ የዩኤስኤም ተከላካዮችን ኳስን ከግቡ መስመር አውጥተዋል፡፡ በ61ኛው ደቂቃ የዩኤስኤሙ አማካይ አሚር ሳዮድ እና ጣሪቅ አህመድ በፈጠሩት ጠብ በቀይ ካርድ ከሜዳ በደቡብ አፍሪካዊው የመሃል ዳኝ ቪክቶር ጎሜዝ ተሰናብተዋል፡፡ አቡራህማን መዛኒ በ87ኛው ደቂቃ ግሩም ግብ አህመድ ኤል ሽናዊ መረብ ላይ አስቆጥሮ ዩኤስኤም አልጀር ወሳኝ ነጥብ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ አነጋጋሪው የዛማሌክ ፕሬዝደንት ሞርታዳ መንሱር ከሽንፈቱ በኃላ ተጫዋቾቻቸውን 100ሺህ የግብፅ ፓውንድ (5ሺ የአሜሪካ ዶላር) ቀጥተዋል፡፡ ምድቡን ዩኤስኤም አልጀር እና አል አሃሊ ትሪፖሊ በእኩል 7 ነጥብ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ የአምና የፍፃሜ ተፋላሚው ዛማሌክ በ5 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ምድብ 3
ቱኒዝ ላይ ኤስፔራንስ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አስናግዶ ያለግብ በአቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ የተሻለ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ብራዚሎቹ በሆሎምፖ ኬካና እና ፐርሲ ታኦ አማካኝነት የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ ፈክረዲን ቤን የሱፍ የኤስፔራንስን የተሻለ እድል የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ አምበሉ ኬካና የመታው ቅጣት ምት ወደ ውጪ ሲወጣ ኮትዲቯራዊው ኩሊባሊ የተሳሳተውን ኳስ ፐርሲ ታኦን ከግብ ጠባቂው ሞይዝ ቤን ሻሪፋ ጋር ቢያገናኘውም ወደ ቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ቋሚነቱ የተመለሰው ቤን ሻሪፋ አምክኖበታል፡፡ የመጨረሻዎቹን 15 ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ በቤን የሱፍ አማካኝነት የግብ እድልን ቢፈጥሩም ዴኒስ ኦኒያንጎ ኳስን ሊያድን ችሏል፡፡ ወሳኙ አጥቂ ጠሃ ያሲን ኬኔሲ የሞከረውን ኳስንም ኦኒያንጎ በቅልጥፍና አምክኗል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ መጀመሪያ ብራዚሎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢወስዱም ወደ ግብ በመሞከሩ በኩል ኤስፔራንሶች የተሻሉ ነበሩ፡፡ በተለይ የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀም ብልጫን የወሰዱት ቀይ እና ወርቃማዎቹ በተደጋጋሚ ለሰንዳውንስን ተከላካዮች ሲያስቸግሩ ተስተውሏል፡፡ የጨዋታው መገባደጃ በተቃረበበት ወቅት የመቀባበያ አማራጮችን በማሳጣት የኤስፔራንስ ተከላካዮች ጨዋታ ነጥብ በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አስችለዋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ኤስፔራንስ በ8 ነጥብ መሪነቱን ሲያጠናክር ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥቡን አስተካክሏል፡፡ በምድብ አምስተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ የሚገጥምበት ጨዋታ ወሳኝ ሆኗል፡፡
ምድብ 4
የካሜሮኑ ኮትን ስፖርት የመጀመሪያው ከቻምፒየንስ ሊግ ምድቡ የተሰናበተ ክለብ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ ጋሮአ ላይ ዛናኮን የገጠመው ኮተን ስፖርት 1-0 ተሸንፏል፡፡ ሴት ሳካላ የዛናኮን የድል ግብ በ91ኛው ደቂቃ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ካሜሮንን ዮርዳኖስ በ2016 ላስተናገደችው የፊፋ የአለም ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ማሳለፍ የቻሉት አሰልጣኝ ቢሪዊ ሚንኬሮ ኮተን ስፖርትን እየመሩ በምድቡ ጨዋታዎች ድል ርቋቸዋል፡፡ ክለቡ ያደረጋቸውን 4 ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፏል፡፡ ምድቡን ባልተጠበቀ መልኩ የተሻለ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የዛምቢያው ዛናኮ በ10 ነጥብ ሲመራ አል አሃሊ በ7 ይከተላል፡፡
የማክሰኞ ውጤቶች
ኤኤስ ቪታ ክለብ 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ 2-0 አል አሃሊ
ኤል ሜሪክ 2-1 ክለብ ፌሮቫሪዮ ደ ቤይራ
የዕረቡ ውጤቶች
ኮተን ስፖርት 0-1 ዛናኮ
አል ሂላል 1-1 ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል
ዩኤስኤም አልጀር 2-0 ዛማሌክ
ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ 0-0 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ
አል አሃሊ ትሪፖሊ 4-2 ካፕስ ዩናይትድ
ቀጣይ ጨዋታዎች
አርብ ሰኔ 23/2009
19፡00 – አል አሃሊ ትሪፖሊ ከ ዩኤስኤም አልጀር
21፡00 – ኤል ሜሪክ ከ አል ሂላል
ቅዳሜ ሰኔ 24/2009
15፡00 – ክለብ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ ከ ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል
15፡00 – ዛናኮ ከ አል አሃሊ
16፡00 – ኮተን ስፖርት ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ
16፡00 – ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ
16፡00 – ኤኤስ ቪታ ክለብ ከ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ