በከፍተኛ ሊግ | የሱሉልታ እና መቀለ ከተማ ጨዋታ ውዝግብ. . .

በሱሉልታ ከተማ እና በመቀለ ከተማ መካከል ጨዋታው እንዲካሄድ አስቀድሞ መርሀ ግብር ወጥቶለት የነበረው ሰኔ 19 ቀን 2009 የነበረ ቢሆንም በጣለው ዝናብ ምክንያት ሜዳው ለጨዋታ ምቹ አይደለም በሚል ጨዋታው ማክሰኞ ሰኔ 20 ረፋድ 05:00 እንዲካሄድ ቢወሰንም በተመሳሳይ ሜዳው ለጨዋታ አመቺ አይደለም በሚል በዚሁ ቀን  09:00 ላይ ሰበታ ከተማ ሜዳ ላይ እንዲካሄድ የዕለቱ ኮሚሽነሮች ወስነው ተለያይተዋል፡፡ በቦታውም መቀለ ከተማዎች ከበርካታ ደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን ቢገኙም ሱሉልታ ከተማዎች የያያ ቪሌጅ ሜዳ ማጫወት ይችል ነበር ፤ ሆኖም ከተቀየረ በነጋታው በሜዳችን መጫወት ይገባናል በማለት ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ጨዋታው ሰኔ 21(ዛሬ) ጠዋት 03:00 እንዲካሄድ የሊግ ኮሚቴ ወሰነ፡፡ ሰበታ ሜዳ ላይ የሚገኙት መቀለ ከተማዎችም ለፌዴሬሽኑ ቅሬታ አቀረቡ።

ዛሬ ሰኔ 21 ጠዋት 03:00 ላይ በሱሉልታው ያያ ቪሌጅ እንዲካሄድ የተወሰነውን ጨዋታ ለማድረግ ሁለቱም ቡድኖች ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ አባል ፣ የሊግ ኮሚቴ አባታት የተገኙ ሲሆን በድጋሚ ሜዳው ለጨዋታ ለማከናወን አመቺ አይደለም በማለት 05:00 ላይ አዲስ አበባ ስታድየም እንዲካሄድ ተወሰናል ።

ከጨዋታው አስቀድሞ በዝናብ ምክንያት ጨዋታው መካሄድ በነበረበት ሰኔ 19 እና 20 ላይ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ሊመሩ የተመደቡት ፌደራል ዳኛ አለማየሁ ለገሰ እና አራተኛ ዳኛ ፌደራል ዳኛ ኢብራሂም አሊጋዝ እንዲሁም ኮምሽነር ይግዛው ተቀይረው በምትካቸው በዋና ዳኝነት ፌደራል ዳኛ ደረጄ ገብሬ በአራተኛ ዳኝነት ፌደራል ዳኛ ፣ዳንኤል ግርማይ በኮምሽነርት ሸረፋ ዴሌቾ የተመደበ ሲሆን በዚህም የዳኛ እና የኮምሽነር ለውጥ ምክንያት ሱሉልታ ከተማዎች ቅሬታቸውን አቅርበዋል ።

05:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የሁለቱም ክለቦች በርካታ ደጋፊዎች በተገኙበት ሞቅ ደመቅ ብሎ የተጀመረው የዕለቱ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጠንካራ ፉክክር ተስተናግዶበት ጎል ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ በቀጠለበት ሰአት 57ኛው ደቂቃ ላይ መቀለ የግብ ክልል ውስጥ የሱሉልታው አጥቂ ቶሎሳ ንጉሴ ጥፋት ተሰርቶብኛል በማለት ቢወድቅም የዕለቱ ዳኛ ደረጄ ገብሬ ሆን ብለህ ነው የወደቅከው በማለት የቢጫ ካርድ ሰጥተውት ጨዋታው በቀጠለበት ቅፅበት በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል መቀለ ከተማን ቀዳሚ የምታደርግ ጎል አስቆጥሯል። በዳኛው ውሳኔ ደስተኛ ያልነበሩት ሱሉልታዎች ዳኛውን በመክበብ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ባለበት ሰአት አምበሉ ቶሎሳ ንጉሴን ጨዋታውን እንዳልመራ አውከኸኛል በማለት በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ አስወጥተውታል።

ከተወሰኑ ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ የቀጠለው ጨዋታ 69ኛው ደቂቃ ላይ አንድ ክስተት ተፈጠረ፡፡ የመቀለው ተጨዋች ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ጎል ቢሞክረውም ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ይወጣል፡፡ ሆኖም የዕለቱ ዳኛ ኳሱን ሲመታው ጥፋት ተሰርቶበታል በሚል የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል፡፡ በዳኛው ውሳኔ የተበሳጩት ሱሉልታዎችም ጨዋታውን አንጫወትም በማለት ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል። የዕለቱ ዳኛ ከኮሚሽነሩ እና የሁለቱም ቡድኖች አምበሎች ጋር ተነጋግረው ጨዋታው 69ኛው ደቂቃ ላይ ሊቋረጥ ችሏል።

ኮሚሽነሩ ከሚያቀርቡት ሪፖርት ተነስቶ የሊግ ኮሚቴው በተቋረጠው ጨዋታ ዙርያ ምን እንደሚወስን ወደፊት የሚገፅ ይሆናል ።

በዚሁ ዕለት አስቀድሞ እንዲካሄድ የተወሰነው የመቀለ ከተማ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ በሱሉልታ እና መቀለ ጨዋታ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ሲሸጋገር ባህርዳር ከተማዎች የቀን ለውጡ የተነገረን በደብዳቤ ሳይሆን በስልክ በመሆኑ ብንቀር ፎርፌ ይሰጥብናል በማለት ባህርዳር ከተማዎች ተገኝተው የነበረ ቢሆንም ጨዋታው ሰኔ 27 እንደሚካሄድ ተነግሯቸው ተመልሰው ሄደዋል።

አሁን ላይ በተገኘው መረጃ መሰረት የዛሬው ጨዋታን የመራው ደረጄ ገብሬ ላይ ቅጣት መጣሉ የተነገረ ሲሆን የውሳኔዎቹን ዝርዝር እንደደረሰን የምናቀርብ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *