የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2009 | በውድድር ዘመኑ መታወስ የሚገባቸው 10 አጋጣሚዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2009 የውድድር ዘመን ከህዳር 3 አንስቶ ሲካሄድ ቆይቶ ሰኔ 17 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት መደምደሙ ይታወሳል፡፡ ፈረሰኞቸ ከ58 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለተከታታይ አራተኛ አመታት እንዲሁም በአጠቃላይ ለ29ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮን ሲሆኑ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጅማሮ ሊጉን የተቀላቀሉት አዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባቡና እንዲሁም በሊጉ ላለፉት 18 የውድድር ዘመናት በተከታታይ በሊጉ የቆየው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሊጉ ተሰናብተዋል፡፡

የሶከር ኢትዮጵያው ዳዊት ጸሀዬም በሊጉ የ30 ሳምንት መርሃ ግብሮች ውስጥ ከተከሰቱት በርካታ ሁነቶች ውስጥ መታወስ ያለባቸውን 10 ጉዳዮች በዚህ መልኩ አሰናድቶታል፡

1. የጌታነህ ከበደ ክብረወሰን

በ1992 ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅን ለቆ መብራት ሀይልን (በአሁኑ አጠራሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ከተቀላቀለ በኃላ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ እጅግ ደማቅ የሆነ አሻራቸውን ማሳረፍ ከቻሉ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዮርዳኖስ አባይ በ1993 የውድድር ዘመን 24 ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ይህ በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ግብ የማስቆጠር ክብረወሰንም ላለፉት 16 አመታት ሳይደፈር እስከ ዘንድሮው የውድድር ዘመን መዝለቅ ችሏል፡፡

በርካታ አጥቂዎች ይህንን በአንድ የውድድር ዘመን 24 ግቦች የማስቆጠር ክብረወሰንን ለመስበር ወይም ለመጋራት እጅግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ታፈሰ ተስፋዬ በሁለት አጋጣሚዎች ፣ አዳነ ግርማ ፣ ሳሙኤል ሳኑሚ እንዲሁም ራሱ ጌታነህ ከበደ ለክብረወሰኑ መቃረብ ችለው ነበር፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን የቀድሞው ክለቡን ደደቢት ዳግም ከሶስት የውድድር ዘመናት የደቡብ አፍሪካ ቆይታ በኃላ የተቀላቀለው ጌታነህ ከበደ በአንድ ጨዋታ ሐት-ትሪክ እንዲሁም በስድስት ጨዋታዎች ላይ ሁለት ሁለት ግቦችን በተጨማሪም በአስር ጨዋታዎች ላይ ደግሞ አንዳንድ ግቦች በድምሩ 25 ግቦችን በማስቆጠር ለ16 አመታት የቆየውን የዮርዳኖስ አባይን ክብረወሰንን መስበር ችሏል፡፡

ጌታነህ ከበደ ቡድኑ በአጠቃላይ በውድድር ዘመኑ ጉዞ ላይ በሊጉ በአጠቃላይ ካስቆጠራቸው 36 ግቦች 25 (69.45%) ማስቆጠር ችሏል፡፡ ጌታነህ ከበደ ቡድኑ ካደረጋቸው 30 የሊግ ጨዋታዎች ላይ በሁሉም ጨዋታች ላይ በመሰለፍ በ17 (58.62%) ጨዋታዎች ላይ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡

እነዚሁ የጌታነህ ከበደ 25 ግቦች ክለቡ ደደቢት በሊጉ በ51 ነጥብ ይዞ በሁለተኛ ደረጃ ሲያጠናቀቅ ክለቡ በአጠቃላይ መሰብሰብ ከቻለው 51 ነጥብ ውስጥ 21 (41.2%) የሚሆነውን ነጥብ ማሳካት የቻሉት በቀጥታ ጌታነህ ከበደ ባስቆጠራቸው ግቦች መሆኑ የተጫዋቾ ግቦች ምን ያህል ለክለቡ ወሳኝ እንደነበሩ ማሳያ ናቸው፡፡

2. የክብረአብ ዳዊት ህልፈት

በዘንድሮው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከተከሰቱ እጅግ አሳዛኝ ዜናዎች መካከል የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታችና የሀዋሳ ከተማ ግብጠባቂ የነበረው ወጣቱ ክብረአብ ዳዊት በህዳር 9 ምሽት በመኖሪያ ቤቱ ከህጻን ልጁ ጋር በተኛበት ወቅት በተነሳ የእሳት አደጋ ምክንያት ከዚህ አለም በሞት የመለየቱ ዜና የስፖርት ቤተሰቡን ከፍተኛ ሀዘንና ድንጋጤ ውስጥ የከተተ አስደንጋጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡ በዚህም ምክንያት ከቀናት በኋላ ጨዋታውን ከንግድ ባንክ ጋር ሊያደርግ የነበረው ሀዋሳ ከተማ በሀዘኑ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩ የሚታወስ ሲሆን በተከታታይ ጨዋታዎችም ሀዋሳ ከተማ ከሀዘን ድባቡ ለመላቀቅ ሲቸገሩ ተስውሎ ነበር፡፡

3. ቅጥ ያጡ የዲሲፕሊን ግድፈቶች

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከወትሮው በተለየ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር እጅግ በርካታ ቅጥ ያጡ የዲሲፕሊን ጥሰቶች የተስተዋለበት ነበር ብሎ ለመናገር ያስደፍራል፡፡ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና ደጋፊዎች በቀጣዩ የውድድር አመት ሊደገሙ የማይገቡ ድርጊቶች ሲፈፅሙም ተስተውሏል፡፡

በ5ኛው ሳምንት ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከመከላከያ ባደረጉት ጨዋታ በተጫዋቾች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት ፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ 8 ቢጫ ካርድ እና 4 ቀይ ካርድ የመዘዙትበት ጨዋታ በሊጉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከተካሄዱ ጨዋታዎች እጅግ በጣም ከፍተኛ ካርዶች የተመዘዙበት ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡

በ22ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ኢትዮጵያ ቡና አስተናግዶ 3-1 በረታበት ጨዋታ ላይ የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች በጋቶች ፓኖም ላይ ከቆዳ ቀለም ጋር የተያያዘ ስድብ መሳደባቸው እና በ72ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ጋቶች ፓኖም በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ሲሰናበት ሜዳ ውስጥ መለያውን አውልቆ ጨዋታውን ከመሩት ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃይለስላሴ ጋር ለዱላ የተጋበዘበት ክስተት ከሊጉ የዘንድሮ መጥፎ ክስተቶች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በ22ኛው ሳምንት የሸገር ደርቢ ላይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአዳነ ግርማ ላይ በሰነዘሯቸው ስድቦች ለቅጣት መዳረጋቸውም የሚታወስ ነው፡፡

በ24ኛው ሳምንት አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ደደቢት 2-0 ከመምራት ተነስቶ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር በ90+7ኛው ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ 2-2 በተለያዩበት ጨዋታ ጌታነህ ከበደ የክለቡን መለያ ቀዶ የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ላይ ወርውሮ የሄደበት አጋጣሚ ደግሞ በብዙሀኑ ዘንድ መነጋገርያ የሆነ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡

በ19ኛው ሳምንት አዲስአበባ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከአዳማ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ፋሲካ አስፋው ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር የፈጠረው ሰጣ ገባ 4 ጨዋታ ቅጣት እንዲተላለፍበት የተደረገውመ በዘንድሮ የውድድር ዘመን ነው፡፡

በ19ኛ ሳምንት ተስተካካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲል ከተማ ጋር 2-2 በተለያዩበት ተስተካካይ ጨዋታ በ82ኛው ደቂቃ ላይ ዘካሪያስ ቱጂን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው አዳነ ግርማ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ላይ ምራቁን የተፋበት ክስተት ሊጉ ካስተናገዳቸው ግድፈቶች አንዱ ነው፡፡

አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በ17ኛው ሳምንት ክለባቸው ደደቢት በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-2 ከተሸነፈ በኃላ በግልፍተኝነት ከጋዜጠኞች ጋር የፈጠሩት አላስፈላጊ ውዝግብ መነጋገርያ ሆኖ መሰንበቱ የሚታወስ ነው፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ንግድ ባንክን 1-0 ባሸነፈበት የሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ብሩኖ ኮኔ ጎል ካስቆጠረ በኋላ ያሳየው የደስታ አገላለፅ ለጸብ የሚያነሳሳ ድርጊት ነበር፡፡ በሁኔታው ብስጭት ውስጥ ከገቡት መካከል ተከላካዩ ቢንያም ሲራጅ በኃይሉ አሰፋን በቡጢ ነርቶ በቀይ ካርድ በወጣበት አሳፋሪ ክስተትም ሊጉ በግድፈት ተጠናቋል፡፡

4.የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች

ደጋፊዎች ለክለባቸው የሜዳ ላይ እና የሜዳ ውጪ ውጤታማነት ያላቸውን ቀጥተኛ አስተዋጽኦ በዘንድሮው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የሊግ ግስጋሴ እንዲሁም አስደናቂ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ጉዞ በስተጀርባ በግልፅ መመልከት ይቻላል፡፡

ፈረሰኞቹ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ከረጅም ዘመናት በኋላ አዲስ ታሪክ መፃፍ ከመቻላቸውም በተጨማሪ የክለቡ የዘመናት ህልም የነበረውንና በቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ተፋላሚ የመሆንን ውጥን ክለቡ ሲያሳካ በሜዳ ላይ ከነበሩት የቡድኑ አባላት በተጨማሪ የደጋፊዎች ሚና እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን እንኳ ቡድናቸው በአሳማኝ ሁኔታ ጨዋታዎች ለማሸነፍ በተቸገረባቸውም ሆነ ውጤት ባጣባቸው አጋጣሚዎች ከቡድናቸው አባላትና አመራሮች ጎን በመሆን እጅግ በሰለጠነ መልኩ ችግሮቻቸውን በውይይት በመፍታት ለቡድናቸው ውጤት ማማር እጅግ ከፍተኛ ሚናን መወጣት ችለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለሀገራችን የእግርኳስ አደጋገፍ ስርአት አዳዲስ የሆኑ የአደጋገፍ ስርአቶችን በየጊዜው በማስተዋወቅም ረገድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደር አይገኝላቸውም፡፡

5. የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን

ውድድሩን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን በውድድሩ ላይ ለሚከሰቱ ጉዳዮች ተጠያቂ ነው፡፡ፌዴሬሽኑ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በእግርኳሳችን ላይ ጥላውን አጥልቶ የነበረውን የስታዲየም ስርአት አልበኝነት ደዌን ከስታዲየሞች በማስወገድ በኩል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለታየው መጠነኛ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ በበጎነቱ የሚወሳ መልካም ስራን ማከናወን ሲችል በተቃራኒው ደግሞ ከዝርክርክ አሰራሮች ራሱን ማጽዳት ባለመቻሉ ተለዋዋጭ ውሳኔዎች እና ጨዋታን የሚያዘገዩ ጉዳዮች አስመልክቶን አልፏል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች ላይ በሚፈፀሙት ጥሰቶች ምክንያት ተጫዋቾች ፣ ደጋፊዎች እና ክለቦች ላይ የጣሉ ቅጣቶች ከገንዘብ ቅጣ በቀር ሌሎቹ ላይ ተደጋጋሚ ማሻሻያዎች ሲደረጉ ማስዋል ተለምዷል፡፡

ከቅጣቶች በዘለለ በ29ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃግብር በሊጉ በወቅቱ በስፋት እየተናፈሰ ይገኝ የነበረውን ላለመውረድ በሚታገሉ ክለቦች መካከል እየተደረገ በነበረው ትንንቅ ላይ የመላቀቅ አዝማሚያ በመታየቱ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎችን በተመሳሳይ ቀንና በእኩል ሰአት ለማድረግ ፌደሬሽኑ ባሳለፍነው ውሳኔ መሠረት በ29ኛው ሳምንት አርብ ሰኔ 9 በቅድሚያ ሰበታ ስታዲየም ላይ በመቀጠል ደግሞ መድን ሜዳ ላይ እንዲካሄድ መርሃግብር የተያዘለት የኢትዮ ኤሌክትሪክና የወልድያ ከተማ ጨዋታ ላይ የተፈጠረው ክስተት አንዱ ተጠቃሽ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡

ልክ እንደሌሎች መሰል ላለመውረድ እየታገሉ ክለቦች እንደሚያደርጉት  ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9 ሰአት እንዲካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ጨዋታ የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች በሰአቱ በሜዳው ቢገኙም ጨዋታው ለማካሄድ በስፍራው ያስፈልጉ የነበሩት የፀጥታ ኃይሎች በወቅቱ በሜዳው ባለመገኘታቸው ጨዋታው በአንድ ሰአት ያክል ዘግይቶ ለመጀመር ተገዷል፡፡

ላለመውረድ ይደረግ በነበረው ከፍተኛ ትግል ውስጥ እጅግ ትልቅ ስፍራ የነበረው ይህን ጨዋታ የመሩት ዳኞች እና ኮሚሽነሩ ጨዋታውን ያለ ፀጥታ ሀይል እንዳይጀመር ውሳኔ ቢያሳልፉም በስፍራው የነበሩት የፌደሬሽን አመራሮች ጨዋታውን እንዲያስጀምሩ ጫና ሲያሳድሩ ተስተውሏል ይህም በስፓርት ቤተሰቡ ዘንድ እጅግ አግራሞትን የጫረ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

ከመድን ሜዳው ትዕይንት ባሻገር አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና እንደዲሁም አአ ላይ ንግደድ ባንክ ከአዳማ ከተማ የተደረጉት ጨዋታዎች በአምቡላንስ በስፍራው ያለመገኘት ምክንያት ዘግይተው የተጀመሩ ጨዋታዎች ነበሩ፡፡

 

6. የሽልማት ስነስርአት

የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከሌሎቹ የውድድር ዘመናት ለየት ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የሆነው ከዚህ ቀደም የሊጉ የመዝጊያ መርሃግብር ከተካሄደ በኃላ አሸናፊው ቡድን ዋንጫ በሚበረከትለት ስነስርአት ላይ ነበር የኮከቦች ሽልማት ይፋ ይደረግ የነበረው፡፡ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን ለየት ባለ መልኩ በመጪው ሀምሌ 25 ለጊዜው ይፋ ባልተደረገ ሆቴል ውስጥ በሚደረግ ልዮ ስነስርአት የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ብቻ ሳይሆን በፌደሬሽኑ ስር ሲካሄዱ በነበሩ የተለያዩ የውድድር ዘርፎች ኮከቦች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በደማቅ ስነስርአት እንዲሚካሄድ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

7. ፋሲል ከተማ እና ደጋፊዎቹ

ፋሲል ከተማ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካደገበት ጊዜ አንስቶ እጅግ ከፍተኛ የሆነ መነቃቃትን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከመፍጠሩ በዘለለ በሊጉ ላይ በጎ ተዕእኖ ማሳረፍ የቻለ ክለብ መሆን ችሏል፡፡

እድሜ ጠገቡ ክለብ ፋሲል ከተማ ሊጉን ከ8 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀላቀለበት የ2009 የውድድር ዘመን በተለይም በመጀመሪያው ዙር በአሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስ እየተመራ እጅግ አስደናቂ ግስጋሴን ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህም የመጀመሪያውን ዙር በ26 ነጥብ ሊጉን ከአናት ከሚመሩት ቡድኖች ውስጥ በአራተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ የመጀመሪያ ዙርን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ በሁለተኛው ዙር መጠነኛ የውጤት መቀዛቀዞችን ቢያስተናግዱም ክስተት በሆኑበት የዘንድሮው የውድድር አመት ጠንካራ የሊጉ ተፎካካሪ በመሆን ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡

ቡድኑ በከፍተኛ ተነስሽነት በሚጫወቱ አንጋፋና ወጣት ተጫዋቾች የተገነባና በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የሚጫወት ጠንካራ ቡድን ሆኖ በተለይ በመጀመሪያ ዙር መቅረብ ችሏል፡፡ ቡድኑ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በሁለተኛው ዙር ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ መጠነኛ የቁጥር መቀነስ ተስተዋለ እንጂ የአፄ ፋሲለደስ ስታዲየም በበርካታ ጨዋታዎች ከአፍ እስከ ገደፉ የክለቡን ቀይና ነጭ መለያ በለበሱ ደጋፊዎች ተጨናንቆ ይስተዋላል፡፡

ቡድኑ ከሜዳ ውጪ በሚያደርገውም ጨዋታዎች የክለቡ ደጋፊዎች እጅግ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ተስተውሏል፡፡ በተለይም ቡድኑ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከበርካቶቹ የአዲስ አበባ ክለቦች በተሻለ እጅግ በርካታ ቁጥር ባላቸው ደጋፊዎች እየታገዘ በሊጉ ጥሩ ግስጋሴን በማድረግ ባደገበት አመት 43 ነጥቦችን በመሰብሰብ በ6ኛ ደረጃ ላይ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

8. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መውረድ

ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን በ1992 የውድድር ዘመን ከተቀላቀለ አንስቶ በቀድሞው አጠራሩ የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር በአሁኑ አጠራሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ውስጥ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆንና በርካታ ለብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት የሰጡ ተጫዋቾችን በማፍራት እስከ አዲሱ ሚሌንየም መጀመርያ መዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ ነገርግን ባለፉት 8 አመታት ተዳክሞ በ2002 የውድድር ዘመን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሻምፒዮን በመሆን በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ መካፈል ከቻለበት ስኬት ውጪ ቡድኑ በሊጉ አጋማሽ ደረጃ ይዞ የሌሎች ክለቦች ደረጃ መዳቢ ከመሆን ይባስ ብሎ ላለፉት ሁለት አመታት ቡድኑ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመዳከር ተገዷል፡፡

ለአመታት በዝውውር መስኮቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ነዋይን ፈሰስ በማድረግ ከውጭ ሀገራትም ጭምር ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድናቸውን መገንባት ቢችልም ቡድኑ ደረጃ ከመመደብ በዘለለ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ለወትሮው ከሚከተሉት የዝውውር ፓሊሲ መጠነኛ ለውጦችን በማድረግ በርካታ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በማሰናበት ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ከሚካሄዱ የተለያዩ የእድሜ እርከን ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪ ብሎም ሻምፒዮን መሆን ከቻሉት የእድሜ እርከን ቡድኖቹ ከ10 የሚበልጡ ታዳጊ ተጫዋቾችን በማሳደግ ቡድኑን እንደ አዲስ በታዳጊዎች ለማዋቀር ጥረት ተደርጓል፡፡

ነገርግን ቡድኑ ውስጥ ካደጉት በርካታ ቁጥር ካላቸው ታዳጊ ተጫዋቾች ውስጥ እጅግ ጥቂቶቹን ያውም ለተወሰኑ ደቂቃዎች የመሰለፍ እድል ቢያገኙም በቡድኑ አሰልጣኝ በኩል ለቡድኑ ውጤት ማጣት በበርካታ አጋጣሚዎች እንደ ምክንያትነት ሲቀርቡ ተደምጧል፡፡ በሁለተኛው ዙር ቡድኑ የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ ወደ 6 የሚጠጉ በሊጉ በበርካታ ክለብ በተጫዋቾችነት ያሳለፉ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ከመጀመሪያው ዙር በተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ እስከ መጨረሻው ሳምንት በሊጉ ለመቆየት ብርቱ ተጋድሎ ቢያደርጉም በስተመጨረሻም 18 የውድድር ዘመናትን ከቆዩበት የኢትዮጵያ ፕሪሕየር ሊግ ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ ተገደዋል፡፡

9. የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች መልእክት እና የመላቀቅ ወሬዎች

በ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዳማ ከተማ በሜዳው ላለመውረድ እየታገለ የነበረውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ባስተናገደበት ጨዋታ ላይ ከጨዋታው መጀመር በፊት የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች በስታዲየሙ እየተዟዟሩ ለተመልካች ያስነበቡት ” ከሙስና የፀዳ ትውልድ ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት” የሚል ፅሁፍ የሰፈረበት ባነር በሊጉ ዘንድሮ ከተከሰቱ አይረሴ ክስተቶች አንዱ ነበር፡፡

ይህንን ጨዋታ ጨምሮ በተለይ በሁለተኛ ዙር ከተካሄዱ በርካታ ጨዋታዎች ጀርባ በማስረጃ ማስደገፍ ያልተቻሉ በርካታ ውጤት ለማስለወጥ የተደረጉ ሸፍጦች እንዲሁም ብልሹ አሰራሮች ስለመኖራቸው የስፖርት ቤተሰቡ በስፋት ሲነጋገርባቸው ቆይቷል፡፡

በዚህም ሂደት ላይ የክለብ አመራሮች በ90 ደቂቃ ውስጥ ሜዳ ላይ ከሚደረገው ያለመሸናነፍ ትንቅንቅ በዘለለ ከጨዋታ በፊት በጠረጴዛ ዙሪያ በሚሸረቡ ደባዎች ውጤትነት ለመለወጥ የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሁም ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ከቡድናቸው ውጤት ማጣት በስተጀርባ የተለያዩ የሴራ ንድፈ ሀሳቦችን ሲያቀርቡ መስማት በዘንድሮው የውድድር ዘመን እንደከዚህ ቀደም የነበሩት የውድድር አመታት ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

10. የደጋፊዎች ተቃውሞ

የዘንድሮው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የበርካታ ክለብ ደጋፊዎች ሰላማዊ የሆኑ ተቃውሞዎችን በክለቦቻቸው ላይ ያንፀባረቁበት ሆኖ አልፏል፡፡

ከነዚህም መካከል በ12ኛ ሳምንት በወቅቱ በነበረው የክለባቸው ውጤት ደስተኛ ያልነበሩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች “ማርት ኑይ አውት” የሚል ባነር ይዘው ክለባቸው ከጅማ አባቡና ጋር በሜዳውና በደጋፊዎቹ ፊት 1-1 በተለያየበት ጨዋታ አስነብበዋል፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በ28ኛው ሳምንት ክለባቸው አዲስ አበባ ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ በወቅቱ ወደ ክለቡ የአሰልጣኝነት መንበር ይመጣል ተብሎ በስፋት እየተነገረለት ከነበረው የቀድሞው ተጫዋቻቸው እና አሰልጣኛቸው ለሆነው ካሳዬ አራጌ ድጋፍ በመስጠት “GK is the only solution ” የሚልን ባነር በስታዲየሙ የተለያዩ ክፍሎች ማስነበብ ችለዋል፡፡

በተጨማሪም በ29ኛው ሳምንት የሊጉ መርሃግብር ከሳምንት በፊት ክለባቸው በኢትዬ ኤሌክትሪክ ተሸንፎ ከጥሎ ማለፍ ውድድር መሰናበቱ ያስከፋቸው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በ29ኛው ሳምንት መርሃግብር ክለባቸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 በተረታበት ጨዋታ በተጫዋቾቻቸው ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞን ከማሰማት በዘለለ በሁለተኛው አጋማሽ 82ኛው ደቂቃ ላይ ስታዲየሙን ሙሉ ለሙሉ ለቀው በመውጣት ተቃውሟቸውን መግለፅ ችለዋል፡፡ በተመሳሳይ በክለባቸው ወቅታዊ ሁኔታ ደስተኛ ያልነበሩት የአርባምንጭ ከተማ ደጋፊዎች በ29ኛ ሳምንት መርሃግብር ቡድናቸው በሜዳው በወላይታ ድቻ 1-0 በተሸነፈበት ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቻቸውና የክለቡ አመራሮች ላይ ተቃውሟቸውን ከማሰማት በዘለለ እነሱም በተመሳሳይ ጨዋታው እየተካሄደ ጨዋታውን አቋርጠው በመሄድ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ዘመናዊው የወልድያ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየምን አስመልክቶን ፣ እዚህ ግባ ባይባልም ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ወጣት ተጫዋቾችን አሳይቶን እንዲሁም የተሻለ የደጋፊዎችን ስርአት ተመልክተን የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጠናቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በስፋትና በልዩነት ለናንተ ስታደርስ የሰነበትችው ሶከር ኢትዮጵያም በዘንድሮ የውድድር ዘመን የታዩ በጎ ባህሎች እንዲበረታቱ እንዲሁም ለእግርኳሱ እድገት ሳንካ የሆኑት አላስፈላጊ ተግባሮች ከእግርኳሱ ተወግደው ቀጣዩ የ2010 የውድድር ዘመን የተሻለ እንዲሆን ትመኛለች፡፡

ለከርሞ ያደርሰን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *