በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አምስት ጨዋታዎች ቅዳሜ ሲደረጉ ከምድብ ሶስት ኤስፔራንስ እና ሰንዳውንስ ከምድቡ ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ ኤትዋል ደ ሳህል ማፑቶ ተጉዞ ያሳከው አንድ ነጥብ ከምድብ አንድ ማለፉን እንዲያረጋግጥ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኤኤስ ቪታ ክለብ እና አል ሂላል ከምድብ መሰናበታቸውን በአምስተኛው የቻምፒየንስ ሊግ የጨዋታ መርሃ ግብር አረጋግጠዋል፡፡
ምድብ 1
ወደ ሞዛምቢክ የተጓዘው ኤትዋል ደ ሳህል ፌሮቫያሪዮ ቤይራን ነጥብ ማስጣሉን ተከትሎ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ባለሜዳው በቺሊቶ ኦማር ድንቅ የ72ኛው ደቂቃ ግብ መሪ ቢሆንም ሳሊም ቤን ቤልጋሲም በፍፁም ቅጣት ምት በ84ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጣሮ የሶሱን ክለብን ወደ ቀጣዩ ዙር አሻግሯል፡፡
ምድቡን ኤትዋል ደ ሳህል በ9 ነጥብ ሲመራ ኤል ሜሪክ በ7 እንዲሁም ፌሮቫያሪዮ በ5 ወደ ሩብ ፍፃሜ የመግባት እድል አላቸው፡፡ ሃያሉ የሱዳን ክለብ አል ሂላል ከምድቡ ተሰናብቷል፡፡ ይህንን ተከትሎ ቱኒዚያዊውን አሰልጣኝ ነቢል ኮኪን አሰናብቷል፡፡
ምድብ 3
ቅዱስ ጊዮርጊስ በወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን በማሜሎዲ ሰንዳውንስ 1-0 ተሸንፎ ለመጀመሪያ ግዜ ከተሳተፈበት የምድብ ውድድር ሲሰናበት ኤኤስ ቪታ ክለብ ከኤስፔራንስ ጋር አቻ መለያየቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹን ተክትሎ ከምድብ ተሰናብቷል፡፡
ላይቤሪያዊው አንቶኒ ላፎር በ86ኛው ደቂቃ ሞሬና ያመቻቸለትን እድል ተጠቅሞ ብራዚሎቹን አዲስ አበባ ላይ ባለድል አድርጓል፡፡ በጨዋታው ላይ በተለይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው አጋማሽ ያመከናቸው እድሎች ዋጋ አስከፍለውታል፡፡ ሳላዲን ሰዒድ እረፍት ከመውጣታቸው በፊት የመታውን የፍፁም ቅጣት ምት የቀድሞ የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ አምክኖበታል፡፡
ኪንሻሳ ላይ ኤስፔራንስ በ10 ተጫዋች ከተጫወተው ኤስ ቪታ ጋር 2-2 ተለያይቶ፡፡ በውድድር አመቱ ድንቅ ብቃቱን ለሃገሩ ቱኒዚያ እንዲሁም ለክለቡ ኤስፔራንስ እያሳየ የሚገኘው ጠሃ ያሲን ኬኒሲ እንግዶቹን በ11ኛው ደቂቃ መሪ ቢያደርግም በትውልድ ዲ.ሪ. ኮንጎ በዜግነት ሩዋንዳዊ የሆነው ዳዲ ቢሮሬ (በቅፅል ስሙ ኢቲኪማ) አከታትሎ ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ባለሜዳውን 2-1 እንዲመራ አስችለውታል፡፡ ሩዲ ማክዊክዊ በሰራው ጥፋት ምክያት በ58ኛው ደቂቃ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወጣ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ኬኔሲ አስቆጥሮ ጨዋታው 2-2 ተጠናቋል፡፡
ምድቡን ኤስፔራንስ በ9 ነጥብ ሲመራ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ5 እንዲሁም ቪታ ክለብ በ4 ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ምድብ 4
አላፊ ቡድኖች ባልተለዩበት በዚህ ምድብ የሪከርድ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አሃሊ ከዛናኮ ጋር አቻ ተለያይቶ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ዋይዳድ ካዛብላንካ ወደ ካሜሮን ተጉዞ እጅግ የተዳከመውን ኮተን ስፖርትን 2-0 ረቷል፡፡
አል አሃሊ በርካታ የግብ እድሎችን ባመከነበት ጨዋታ የዛምቢያው ዛናኮ አንድ ነጥብ በሜዳው ማግኘት ችሏል፡፡ ዛናኮ ውጤቱን ተከትሎ የምድብ መሪነቱን ሲያጠናክር ባለልተጠበቀ መልኩ ሃያል ከሆኑት የሰሜን አፍሪካ ክለቦች አንዱ ከዚህ ምድብ የማለፍ እድሉ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
የጨዋታ እና የሙከራ ብልጫ የነበረው የሞሮኮው ቻምፒዮን ዋይዳድ ካዛብላንካ ኮተን ስፖርትን አሸንፏል፡፡ አችራፍ ቤንቻጉሪ እና ነይም የግቦቹ ባለቤቶች ናቸው፡፡ አምስት ጨዋታ በተከታታይ የተሸነፈው ኮተን ስፖርት አስከፊ የቻምፒየንስ ሊጉ ካደረገ በኃላ አስቀድሞ ከምድብ መሰናበቱን ከሁለት ሳምንታት በፊት አረጋግጧል፡፡
ምድቡን ዛናኮ በ11 ነጥብ ሲመራ ዋይዳድ በ9 ነጥብ ሁለተኛ ነው፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የካይሮ ሃያል በ8 ነጥብ ሶስተኛ ነው፡፡ ኮተን ስፖርት ያለምንም ነጥብ ግርጌ ላይ ይገኛል፡፡
የአርብ ውጤት
ኤል ሜሪክ 2-1 አል ሂላል
አል አሃሊ ትሪፖሊ 1-1 ዩኤስኤም አልጀር
የቅዳሜ ጨዋታ
ክለብ ፌሬቫያሪዮ ደ ቤይራ 1-1 ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል
ዛናኮ 0-0 አል አሃሊ
ኮተን ስፖርት 0-2 ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ
ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-1 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ
ኤኤስ ቪታ ክለብ 2-2 ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ
የእሁድ ጨዋታ
15፡00 – ካፕስ ዩናይትድ ከ ዛማሌክ