የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ በአአ ስታድየም ተካሂደው ወላይታ ድቻ እና መከላከያ ወደ ፍጻሜው ያሻገራቸውን ድል አስመዝግበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ስታድየም ቀዝቃዛ አየር የታጀበውና በርካታ ተመልካች ባልተከታተው የወልድያ እና መከላከያ ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ ነፃ የኳስ ፍሰት ፣ የተደራጀ እንቅስቃሴ እና ጥሩ የመሸናነፍ ፍላጎት ታይቶበታል፡፡
መከላከያዎች በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ቢሆኑም በተለይ ባዬ ገዛህኝ እና ሳሙኤል ታዬ ይፈጥሩት የነበረውን ጎል የማግባት አጋጣሚ ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት የወልድያ የተደራጀ የመከላከል ዘዴን ሰብሮ ጎል ማስቆጠር ተስኗቸው ታይቷል፡፡ በንፃሩ ወልድያ ለአንዷለም ንጉሴ በረጅሙ በሚጣሉ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ቢታይም የተሳካ ጠንካራ የጎል እድል መፍጠር አልቻሉም። ጨዋታውም ምንም አይነት ጎል ሳይስተናገድበት ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ማራኪ የኳስ ፍሰት በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ መከላከያዎች ተጭነው ሲጫወቱ በዋናነት ባዬ ገዛህኝ እና መስፍን ኪዳኔ የሞከሯቸው እንዲሁም ሳሙኤል ታዬ ከርቀት የመታው ኳስ አግዳሚውን ታኮ የወጣበት ሙከራየሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በተደጋጋሚ ተመላልሰው የወልድያን የግብ ክልል የፈተሹት መከላከያዎች ጥረታቸው ተሳክቶላቸው ከረጅም ጊዜ ጉዳት መልስ ለመከላከያ ጥሩ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኘው ባዬ ገዛህኝ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ 81ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ በመግጨት ጎል አስቆጥሮ መከላከያን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።
ወልድያ የአቻነት ጎል በመፈለግ በቀሩት ደቂቃዎች ተጭኖ በመጫወት ሀብታሙ ሸዋለም ከርቀት መሬት ለመሬት መቶ ይድነቃቸው ኪዳኔ እንደምንም ያዳነበት እንዲሁም የዳኛው የጨዋታ ማጠናቀቂያ ፊሽካ እየተጠበቀ ባለበት ሁኔታ ወልድያን አቻ ማድረግ የሚችል አጋጣሚ ያሬድ ብርሃኑ ብቻውን ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጠረ ሲባል ከግቡ አግዳሚ በላይ የወጣው ኳስ ለወልድያዎች የተሻለ የጎል እድል ነበር።
ጨዋታው በመከላከያ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ጦረ ለ3ኛ ተከታታይ የውድድር ዘመን የጥሎ ማለፍ ፍፃሜ ተፋላሚ ሆኗል፡፡
10:30 ላይ ሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በወላይታ ድቻ እና ጅማ አባቡና መካከል ተካሂዶ ድቻ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለፍፃሜ ዋንጫ ማለፉን አረጋግጧል ። ከመጀመርያው በተሻለ በቁጥር በርከት ያለ ተመልካች በተከታተለው ጨዋታ ከመጀመርያው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ የኋላ የኋላ ተጋግሎ ሲቀጥል ከወላይታ ድቻ በተሻለ ጅማ አባ ቡናዎች የመሀል ሜዳ ክፍሉን በሀይደር ሸረፋ እና በዳዊት ተፈራ አማካኝነት ጨዋታውን ተቆጣጥረው ተጫውተዋል፡፡
ጅማዎች የወሰዱትን ብልጫ በመጠቀም የግብ እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር፡፡ በድሉ መርዕድ ነፃ ሆኖ ለማስቆጠር በተመቻቸ አቋቋም ላይ ያገኘውን ኳስ ፈቱዲን ጀማል በፍጥነት ከኋላው መጥቶ ተደርቦ ያወጣበት እንዲሁም የወንድወሰን አሸናፊን ከግቡ ክልል መውጣት ተመልክቶ ከሳጥን ውጭ ዳዊት በግራ እግሩ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ሙከራ ጅማ አባቡና የፈጠራቸው ጥሩ የሚባሉ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ። ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ አብዛኛውን ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክፍል በመገደብ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የጎል እድል ለመፍጠር ቢሞክሩም የተሰካ ሳይሆን ያለ ጎል እረፍት ወጥተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የሜዳው የመሀለኛ ክፍል በመጨቀይቱ ምክንያት በመጀመርያው አጋማሽ በመሀል ሜዳው ክፍል ላይ ብልጫ ወስደው የነበሩት ጅማ አባቡናዎች ኳሱን እንደ ልብ አንሸራሽረው ለመጫወት ሲቸገሩ በጉልበት እና ፍጥነት ከጅማ አባ ቡና የተሻሉት ድቻዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ተሳክቶ 66ኛው ደቂቃ ላይ ፈቱዲን ጀማል ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አላዛር ፋሲካ ወደ ግብነት በመቀየር ድቻን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማ አባ ቡናዎች የአጥቂ አማራጫቸውን ተጨዋቾች በመቀየር በማስፋት የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ ቀርቷል። ጨዋታውም በወላይታ ድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቆ ለመጀመርያ ጊዜ ለጥሎ ማለፍ ፍጻሜ መድረስ ችለዋል፡፡
የጥሎ ማለፉ የፍጻሜ ጨዋተ በመጪው አርብ ሰኔ 30 ቀን 2009 በአዲስ አበባ ስታድየም ይደረጋል፡፡