የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2009 የውድድር አመት መጠናቀቅን ተከትሎ ሶከር ኢትዮጵያ የውድድር ዘመኑን ምርጥ 10 ዝርዝር ጥንቅርን በተከታታይ ክፍሎች በማስቃኘት ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህ ጥንቅርም በክረምቱ ከተከናወኑ ዝውውሮች መካከል ስኬታማ የሚባሉትን 10 ዝውውሮችን እንመለከታለን፡፡
1. ጌታነህ ከበደ
ጌታነህ ከበደ ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት እምብዛም ስኬታማ ካልነበረ የሶስት አመታት የደቡብ አፍሪካ ፕሪምየር ሶከር ሊግ ቆይታ በኃላ የሀገራችን የተጫዋቾች ዝውውር ከብረ ወሰን በነበረ ከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ የቀድሞው ክለቡ ደደቢትን ዳግም ተቀላቅሏል፡፡
ጌታነህ በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ሐት-ትሪክ በመስራት የከፈተውን የግብ አካውንት ወላይታ ሶዶ ላይ በመጨረሻው ሳምንት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች በማሳረግ በአጠቃላይ በሊጉ 25 ግቦችን በማምረት ከተከታዩ ሰልሀዲን ሰኢድ በ10 ግቦች በመራቅ በሊጉ ለ16 አመታት በዮርዳኖስ አባይን በ1993 የውድድር ዘመን 24 ግቦችን በአንድ የውድድር ዘመን በርካታ ግብ የማስቆጠር ክብረወሰንን በመስበር ጭምር የጣምራ ስኬት ባለቤት በመሆን በግሉ እጅግ ስኬታማ የውድድር ዘመንን ማሳለፍ ችሏል፡፡
በሊጉ ያስቆጠራቸው ግቦች ደደቢት በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ሲረዱት እንደ ቡድን በተለይ በፈጠራ ብቃት ረገድ እጅግ ደካማ ከነበረው የዘንድሮው የደደቢት የቡድን ስብስብ ይህ ነው የሚባል የጠራ የኳስ አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ ይህን ያህል ግቦችን ማስቆጠር መቻሉ በበርካቶች ዘንድ አድናቆት አስችሮታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ አለኝ ብላ ከምትመካባቸው አጥቂዎች መካከል ግንባር ቀደም የሆነው ጌታነህ ከበደ ከወዲሁ ከበርካታ የባህርማዶ ክለቦች ጋር ስሙ እየተያያዘ ሲገኝ በዘንድሮው የውድድር ዘመን እጅግ ስኬታማው ተጫዋች ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
2. አብዱልከሪም ኒኪማ
ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት በተለይ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ስብስብ ዋንኛ ድክመት እንደሆነ ሲነገር በነበረው የአማካይ ክፍሉ ላይ ከሀገር ቤት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ጥረት ቢያደርግም ሳይሳኩ በመቅረታቸው ፊቱን ወደ ባህርማዶ ተጫዋቾች በማዞር በርካታ ተጫዋቾችን ከውጪ በማስመጣት መሞከር ችሏል፡፡
ከነዚህም ተጫዋቾች መካከል በሆላንዳዊዉ አሰልጣኝ ማርት ኑይ እምነት ተጥሎባቸው ቡድኑን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አብዱልከሪም ኒኪማ የቴክኒክ ችሎታውንና ጥሩ የእይታ ክህሎቱን በመጠቀም በተለይ ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር ላይ ከፍተኛ ሚናን መጫወት ችሏል፡፡
ተጫዋቾቹም ከአጥቂ ጀርባ በሚገኘው ስፍራ በአመዛኙ ቡድኑ በሚከተለው የ4-3-3 ቅርፅ ላይ ለአጥቂዎችም ከሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾች በተሻለ የግብ እድል በመፍጠር እንዲሁም በአንዳንድ ጨዋታዎች በመስመር አጥቂነት በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ በቀጥተኛ አጨዋወት ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት እንዲሁም ከመስመር ወደ መሀል እየሰበረ በመግባት አደጋዎችን በመፍጠር በኩል የተዋጣለት ነበር፡፡
ተጫዋቹ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ አመት ቆይታው ጥሩ የሚባልን እንቅስቃሴ ከማሳየት አልፎ ሁለት ወሳኝ የሆኑ ግሩም ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
4. ጃኮ አራፋት
ባለፉት ጥቂት አመታት ሀዋሳ ከተማዎች አጥተውት የነበረውን ሁነኛ የፊት አጥቂ ችግር የቀረፈ ተጫዋች ነው ለማለት ያስችላል፡፡
ታታሪው አጥቂ ጃኮ አራፋት በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን ቆይታው 12 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተቃራኒ ቡድን የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾችን እረፍት በመንሳት እንዲሁም ከኳስ ውጪ በሚያደርገው እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ለሌሎች የቡድን አጋሮቹ የሚሆኑ ክፍተቶችን በመፍጠር ረገድ እጅግ የተዋጣለት ነበር፡፡
በበርካታ የአውሮፓ ክለቦች የመጫወት የካበተ ልምድ ያለውና በዘንድሮው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚጫወቱ የባህርማዶ ተጫዋቾች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ቶጎዋዊው አጥቂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከባህር ማዶ ወደ ሀገራችን ክለቦች ከተዘዋወሩ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾች እጅግ የተሻለ ስለመሆኑም በርካቶች ምስክረነታቸውን ሰጥተውታል፡፡
4. ክሪዚስተም ንታንቢ
ዩጋንዳዊዉ የመሀል ሜዳ ስፍራ ተጫዋች በውድድር ዘመኑ ጅማሮ ጅማ አባቡናን መቀላቀል ቢችልም በተለይ ቡድኑ በተሳተፈበት 11ኛው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ባሳየው ደካማ እንቅስቃሴ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ዘንድ የተጫዋቹን የጅማ አባቡና ዝውውር ጥያቄ ውስጥ ከተውት ነበር፡፡ ነገር ግን በጊዜ ሂደት ክሪዚስተም ንታንቢ በሚሰለፍበት የተከላካይ አማካይ ስፍራ ለቡድኑ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች በቂ የሆነ ሽፋን ከመስጠት በዘለለ በቡድኑ የኳስ ስርጭት በጉልህ የሚታይ ድርሻን ማበርከት ችሏል፡፡
በሁለተኛው ዙር ቡድኑ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ እየተመራ ከአዳማ ከተማ በውሰት ውል በፈረመው ኄኖክ ካሳሁን ምክንያት አሰልጣኙ ባደረጉት መጠነኛ የተጫዋቾች የሚና ሽግሽግ ቀድሞ ከሚጫወትበት የተከላካይ አማካይነት ስፍራ ወደፊት በመጠጋት መጫወት ችሏል፡፡ ይህንን አዲሱን ሚናውን በፍጥነት በመላመድ በሁለተኛው ዙር እጅግ የተለየ ተጫዋች ሆኖ መቅረብ ችሏል፡፡ በዚህም ንታምቢ በቡድኑ የሁለተኛው ዙር ላለመውረድ እስከ መጨረሻ ሳምንት ባደረጉት ትግል ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል፡፡
5. ፍሬው ሰለሞን
ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት ከርካታ የሊጉ ኃያላን ቡድኖች ጋር ስሙ በስፋት ሲያያዝ ቢከርምም በመጨረሻም ሳይጠበቅ የትውልድ ከተማውን ክለብ ሀዋሳ ከተማ መቀላቀል ችሏል፡፡
በሊጉ በአሁኑ ወቅት ከአጥቂ ጀርባ በሚገኘው ስፍራ ላይ ከሚጫወቱና እጅግ የላቀ የቴክኒክና የፈጠራ ብቃት ካላቸው ተጫዋቾች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ፍሬው ሰለሞን በግሉ በዘንድሮው የውድድር ዘመን 10 ግቦችን ከማስቆጠሩም በዘለለ በርካታ ለግብ የሚሆኑ ጣጣቸውን የጨረሱ የመጨረሻ ኳሶችን በማቀበል በግች ላይ ባለው ተሳትፎ የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡
ምንም እንኳን ክለቡ ሀዋሳ ከተማ እንደያዘው የቡድን ስብስብ ጥራት አመርቂ የሚባል ውጤትን ባያስመዘግብም በግሉ እንደከዚህ ቀደሞ እንደነበሩት የውድድር አመታት የተሳካ ጊዜን ማሳለፍ ችሏል፡፡
6. አበበ ጥላሁን
በዘንድሮው የውድድር ዘመን እጅግ ወጥ የሆነ የውድድር ዘመን ካሳለፉ ተከላካዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ባሳለፍነው ክረምት የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት አርባምንጭ ከተማን ለቆ ሲዳማ ቡናን መቀላቀል የቻለው አበበ ጥላሁን፡፡
የአየር ላይ ኳሶች ላይ ባለው የበላይነት እንዲሁም በሊጉ ከሚጫወቱ ጥቂት ከኳስ ጋር ምቾት ከሚሰማቸው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አበበ ከኬኒያዊዉ የቡድን አጋሩ ሰንደይ ሙቱኩ ጋር በመሆን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሶስተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው የጠንካራው የሲዳማ ቡና የተከላካይ ስፍራ ደጀን መሆን ችሏል፡፡
በመከላከሉ በኩል ካለው የመከላከል ጥንካሬ በዘለለ ቡድኑ ኳስን ከኃላ መስርቶ ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ጉልህ ሚናም መወጣትን ችሏል፡፡
7. አምሳሉ ጥላሁን
የዳሽን ቢራን መፍረስ ተከትሎ ወደ ከተማው ሌላኛው ቡድን ፋሲል ከተማ መቀላቀል የቻለው የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን በዘንድሮው የውድድር ዘመን በቦታው ላይ ወደር የማይገኝለትን እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ ክስተት ለነበሩት ነጭና ቀይ ለባሾቹ አፄዎቹ ቡድን ውስጥ ጠንካራ እንቅስቃሴን ማሳየት ችሏል ፤ በግራ መስመር በሜዳው ቁመት በሚገኘው የሜዳ ክፍል በሙሉ በከፍተኛ ብርታት በቡድኑ የመከላከል ሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ በጉልህ አሻራውን ማኖር ችሏል፡፡
በተለይ ፈጣን በሆነ መልሶ ማጥቃት በሚታወቁት ፋሲል ከተማዎች የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በሚገኙበት ወቅት በፍጥነት ራሱን ዝግጁ በማድረግ ፍጥነቱን በመጠቀም በተደጋጋሚ የግራ መስመር በኩል ቡድኑ ጥቃቶችን እንዲሰነዝር አስችሏል፡፡
ተደናቂ እንቅስቃሴን ዘንድሮ ማሳየት የቻለው አምሳሉ ጥላሁን በግሉ ውጤታማ የውድድር ዘመን ከማሳለፉ በዘለለ የሊጉ ክስተት ለነበሩት አፄዎቹ አስደናቂ የሊግ ግስጋሴ ውስጥ ዋንኛ ተዋናይ በመሆን ስኬታማ የውድድር ዘመንን አሳልፏል፡፡
8. አቤል ማሞ
በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ካሳለፍነው አመት ጀምሮ ጥሩ ስምን መገንባት ከቻሉ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ የሆነው አቤል ባሳለፍነው ክረምት የዝውውር መስኮት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የነበረው ሙገር ሲሚንቶን ለቆ መከላከያን ከተቀላቀለ በኃላ የተሳካ የውድድር ዘመንን ማሳለፍ ችሏል፡፡
መከላከያዎች የቡድናቸው ዋንኛ ግብ ጠባቂ የነበረው ጀማል ጣሰው ወደ ጅማ አባቡና ማምራቱን ተከትሎ ሊፈጠር ይችል የነበረውን ክፍተት በሚገባ ሞልቷል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን አቤል ማሞ የፍጹም ቅጣት ምቶቸችን ጨምሮ በርካታ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ሙከራዎችን በማዳን ካለፉት አመታት እጅግ የወረደው መከላከያን በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ እንዲቀመጥ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡
9. ሐብታሙ ወልዴ
እጅግ ደካማ ከነበረውና ላለመውረድ ለጥቂት በ11ኛው ሰአት ላይ ከተረፈው የድሬዳዋ ከተማ የቡድን ስብስብ ውስጥ እንደ በጎ ጎን ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች ውስጥ ባሳለፍነው የክረምት የዝውውር መስኮት በከፍተኛ ሊግ ድንቅ እንቅስቃሴን ያሳየበት ኢትዮጵያ መድንን ለቆ ድሬዳዋ ከተማን የተቀላቀለው ሐብታሙ ወልዴ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
ሐብታሙ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ እጅግ ደካማ የውድድር ዘመን ባሳለፈው ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ በግሉ 8 ግቦችን በሊጉ በማስቆጠር የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ማጠናቀቅ ችሏል፡፡
እጅግ ከፍተኛ በሆነ የተተኪ አጥቂዎች ችግር እየታመሰ በሚገኘው የሀገራችን እግርኳስ ተጫዋቹ ጠንክሮ የሚሰራ ከሆነ ለወደፊቱ ከዚህ የተሻለ ጥሩ አጥቂ የመሆን አቅም እንዳለው በአንድ አመት የሊጉ ቆይታው ማሳየት ችሏል፡፡
10. አንዷለም ንጉሴ
አንጋፋው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ ባሳለፍነው ክረምት ሲዳማ ቡናን ለቆ ወልድያን በመቀላቀል በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እጅግ በርካታ አመታት ልምዱን በመጠቀም ወልዲያን ከወራጅነት ስጋት በመላቀቅ በሊጉ ወገብ እንዲጨርስ አስችሏል፡፡
እያደረ እየጎመራ የሚገኘው አጥቂው በጨዋታ ከአንድ ጎል በላይ ማስቆጠር በሚቸገረው ወልድያ 10 የሊግ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ ቡድኑ ካለበት የስብስብ ጥልቀት ችግር የተነሳ በአመዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ እጅግ ከፍተኛ ግልጋሎትን ማበርከትም ችሏል፡፡
ሌሎች የሚጠቀሱ ምርጥ ዝውውሮች
አዳማ ከተማን ለቆ በክረምቱ ወደ አርባምንጭ የተዛወረው ወንድሜነህ ዘሪሁን በተለይ በመጀመርያው የውድድር ዘመን አጋማሽ ምርጥ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ የሲዳማ ቡናው ሰንደይ ሙቱኩ እና የደደቢቱ ካድር ኩሊባሊ ወጥ አቋም በማሳየት ድንቅ አመት አሳልፈዋል፡፡ የወልድያው ያሬድ ዘውድነህ ፣ የአዳማ ከተማዎቹ ሙጂብ ቃሲም እና ዳዋ ሁቴሳ ፣ የሀዋሳ ከተማው መሀመድ ሲይላ እንዲሁም የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ኢብራሂም ፎፋና ሌሎች መልካም የሚባሉ ዝውውሮች ናቸው፡፡