በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ ወደ ቱኒዝ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 ውጤት በኤስፔራንስ ተሸንፎ ውድድሩን አጠናቋል፡፡ በምድቡ ሌላ ጨዋታ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከቪታ ክለብ ጋር 1-1 ተለያይተዋል፡፡ ውጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ በግብ ክፍያ በቪታ ክለብ ቢበለጥም እርስበእርስ ተገናኝቶ ኪንሻሳ ላይ ያስቆጠራት ግብ ምድቡን በ3ኛ ደረጃነት እንዲያጠናቅቅ አስችላለች፡፡
ፈረሰኞቹ ከሳምንት በፊት ከቻምፒየንስ ሊጉ መውደቃቸውን በማረጋገጣቸው ጨዋታው ይበልጥ አስፈላጊ የነበረው ምድቡን በመሪነት ለማጠናቀቅ ከሰንዳውንስ ጋር እየተፎካከረ ለነበረው ኤስፔራንስ ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለጫና ወደ ጨዋታው ቢመጣም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የወረደ አቋምን አሳይቷል፡፡ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በኤስፔራንስ ተጫዋቾች እጅ ከመገኘቱ ባሻገር የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ኳስን ሲይዙ በቀላሉ መልሰው መነጠቃቸው እና ኳስን ይዘው የሚቆዩበት ግዜም አጭር ነበር፡፡ የግራ መስመር ተመላላሹ ካሊል ቻማም በ29ኛው ደቂቃ አክርሮ በመምታት ኤስፔራንስ ቀዳሚ ሲያደርግ ቢለል ሜጅሪ አኒስ ባድሪ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ በ36ኛው ደቂቃ ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ባለሜዳዎቹ ክለቦቹ ለእረፍት ከመውጣታቸው አስቀድሞ ሌላ ሶስተኛ ግብ በፋክረዲን ቤን የሱፍ አማካኝነት ቢያክልሙ ቤን የሱፍ ከጨዋታ አቋቋም ውጪ በመገኘቱ ግቧ ሳትፀድቅ ቀርታለች፡፡
ከእረፍት መልስ የኤስፔራንሶች ብልጫ የቀጠለ ሲሆን በሙከራም ረገድ ፈረሰኞቹ ከመጀመሪያው 45 የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ሊጠቀስ የሚችለው በ54ኛው ደቂቃ ፕሪንስ ዋንጎ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሞይዝ ቤንሻሪፋ የያዘውንብቻ ነው፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ኮትዲቯራዊው አማካይ ፋውሴኒ ኩሊባሊ በጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት ያስጀመረውን ኳስ በግሩም ቅብብል ሃይታም ጁኒ እግርስር ደርሳ ቱኒዚያዊው ጁኒ የሮበርት ኦዶንካራ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ አሊ ሜቻኒ ደግሞ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ በሚጠበቅበት ወቅት ተጨማሪ ግብ አክሎ ኤስፔራንስ 4-0 ጨዋታውን ማሸነፍ ችሏል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ ምድቡን በአምስት በሶስተኛነት ያጠናቀቀ ሲሆን ሰባት ግቦችን አስተናግዶ ሁለት ግቦችን ብቻ በተጋጣሚዎቹ መረብ ላይ አሳርፏል፡፡ ክለቡ የምድብ ተፋላሚ በመሆኑ የ550ሺ የአሜሪካ ዶላር ሽልማት ከካፍ የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ምድቡን ኤስፔራንስ በ12 ነጥብ መሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ በ9 ነጥብ ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል፡፡
የጨዋታው ዋና ዋና እንቅስቃሴዎች | LINK