2ኛ ዙር የኢትዮዽያ ቡና ዓመታዊ የቤተሰብ ሩጫ “በስፖርታዊ ጨዋነት ለስታድየሜ ግንባታ እሮጣለው” እና “ሜዳችን በራሳችን!” በሚል መሪ ቃል ሐምሌ 9 ቀን 2009 እንደሚደረግ ክለቡ ዛሬ በሂልተን አዲስ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮዽያ ቡና የስፖርት ክለብ አመራር አካላት ፣ የደጋፊ ማህበሩ ኃላፊዎች እንዲሁም ደጋፊዎች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት ዛሬ በ04:00 በሂልተን አዲስ በተሰጠው መግለጫ በርካታ ጉዳዮች የተነሰ ሲሆን በዚህ ፅሁፍ ከሩጫው ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጠቅለል አድርገን አቅርበንላችኋል፡፡
የክለቡን ሕብረ ዝማሬ በጋራ በመሆን በመዘመር በተጀመረው ጋዜጣዊ መግለጫ የክለቡ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አቶ ይስማሸዋ ስዩም ሩጫው የሚካሄድበት አላማ እና በውስጡ ስለያዘው ቁምነገር በዝርዝር ተናግረዋል።
መቼ? የት? የተሳታፊ ብዛት?
የዘንድሮው ሩጫ ለ2ኛ ዙር የኢትዮዽያ ቡና ቤተሰብ ዓመታዊ ሩጫ የፊታችን እሁድ ሐምሌ 9 ቀን 2009 ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በ67 ቁጥር ባስ ማዞርያ መነሻውን በማድረግ በለቡ መብራት ሀይል ፣ በጀርመን አደባባይ ፣ በጀሞ አድርጎ የክለቡ ሜዳ ላይ ፍፃሜውን የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ካርታም ተዘጋጅቶለታል፡፡ ሩጫው ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 10,000 ተሳታፊዎች በእለቱ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እስካሁን ባለን መረጃም 8,000 ደጋፊዎች ተመዝግበዋል ፤ ቀሪው 2000 ደግሞ በሚቀሩት ቀናት ተሽጦ ይጠናቀቃል፡፡
የመሮጫ ቲሸርቱን የሸጥነው በኔትዎርክ ሲስተም ሲሆን ከነገ (ሀሙስ) ጀምሮ ቲሸርት ለተሳታፊዎች የምናድል ይሆናል፡፡ ከማደሉ ጎን ለጎን አንድ ተሳታፊ በሩጫው ወቅት ማድረግ የሚገባው እና ማድረግ የሌለበትን ጉዳዮች የያዘ ደንብ አብረን እንሰጣለን፡፡
በሩጫው ላይ ሰለሚኖረው የተለየ መርሐግብር እና የፀጥታ ጉዳዮች
ሩጫውን ለማድመቅ የተለያዩ ዝግጅቶች ይኖራሉ፡፡ በመከላከያ የማርሽ ባንድ በታገዘው ሩጫ ላይ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆነችው ጀግናዋ አትሌት ሻለቃ ደራርቱ ቱሉ ሩጫውን የምታስጀምርም ይሆናል፡፡ ከሩጫው ፍፃሜ በኋላ ለአሸናፊዎች ሽልማት የሚሆነው ከቡና ጋር ታሪካቸው ተሰርቶ ‘ቡናችን’ በተሰኘውና በጄቲቪ በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ይቀርባሉ፡፡ በድንኳኖች የተለያዩ መሰናዶዎችን የምናዘጋጅ ሲሆን ለጠንቃቄ እንዲረዳ አንቡላንስ ተዘጋጅቷል፡፡ በፀጥታው ረገድ ከፖሊስ ኃይል በተጨማሪ የደጋፊ ማህበሩ አባል የሆኑ ከ50 ያላነሱ በሩጫው ላይ የሚሳተፉ ፀጥታውን የሚያስከብሩ አባላት ተዘጋጅተዋል፡፡
የሩጫው አላማ
ከእነዚህ የሩጫ ቲሸርቶች ሽያጭ እና በስፖንሰር ስምምነት የሚገኙ ገቢዎች ተሰብስበው ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ይገኛል ተብሎ ይገመታል፡፡
ክለቡ ለሚያስገነባው ዘመናዊ ስታድየም መንግስት ለክለቡ በሰጠው 35ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ጀሞ አካባቢ ይገነባል፡፡ ከ35-40 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ይኖረዋል ተብሎ የሚገመተውን ስታድየም ለመስራት አስቀድሞ የወጣውን ዲዛይን እንደገና መከለስ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት ጨረታ አውጥተናል፡፡
የስታድየሙን ግንባታ ለመጨረስ 300 ሚልዮን ብር እና (በ2010 ተጀምሮ) አምስት አመት ይፈጃል፡፡ ወጪውንም “ሜዳችን በራሳችን!” በሚል መርህ በክለቡ ቤተሰቦች ብቻ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በሩጫው የሚገኘው ጠቅላላ ገቢም ለስታድየሙ ግንባታ የሚውል ሲሆን በዕለቱ በሚገኙት እንግዶች አማካኝነት የመሰረት ድንጋይ ይቀመጣል።
በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በመተራስ ከተሳታፊዎች ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ከመድረኩም ምላሽ ተሰቶበታል፡፡ ሩጫው በሰላም ያለ ምንም ስጋት እንዲጠናቀቅ ምን ታስቧል? የስታድየሙ የመሰረት ድንጋይ ከመጣል በላይ በወጣለት ዕቅድ መሰረት አምስት አመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ምን ታስቧል? የስታድየሙ ዲዛይን የቡና አሻራ እንዲኖርበት ምን የታሰቡ ነገሮች አሉ? የሚሉና በክለቡ ወቅታዊ ውጤት መጥፋት ጋር ተየይዞ የቀረቡ ጥያቄዎችን መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እና የሩጫው አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ይስማሸዋ ስዩም ምላሽ ሰተውበታል ።
“በጥንቃቄ በከፍተኛ ደረጃ ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት አይኖርም፡፡ አስፈላጊውን ዝግጅት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሰራን በመሆኑ ምንም የሚያሳስብ ነገር የለም፡፡ ”
“በኢትዮዽያ ቡና ከሜዳ ውጭ አቅደን ያልሰራነው ነገር የለም፡፡ ያቀድነውን በሙሉ አሳክተናል ፤ የተጨዋቾች ማረፊያ ነበር እሱን ገንብተን ጨርሰናል፡፡ የሬድዮ ፣ የቲቪ ፕሮግራም አስበን እሱንም አሳክተናል፡፡ እኛ አቅደን ያላሳካነው ስታድየም ብቻ ነው። ስለሆነም በምንችለው አቅም ከደጋፊዎቻችን ጋር በመሆን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጠንክረን እንሰራለን።”
“በስታድየሙ ዲዛይን ላይ እና በአነስተኛ ወጪ ለማጠናቀቅ አውሮፓ ላይ ከሚገኙ የዘመናዊ ስታድየም ባለቤት ክለቦች ሰፊ ልምድ ወስደናል፡፡ ዲዛይኑም የክለቡን ታሪክ እና አሸራ የሚገልፅ ይሆናል፡፡”
በመጨረሻም ለዚህ የሩጫ ውድድር መሳካት ድጋፍ ላደረጉት አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበው ይህን ታሪካዊ ስቴዲዮም ለመገንባት ሁሉም ደጋፊዎች ከጎናቸው እንደሚቆሙ ገልፀዋል
*ማስታወሻ
ዛሬ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በክለቡ የውጤት ቀውስ እና እያጋጠሙት ስላሉት ችግሮች በቀጣይ አመት ክለቡ ስለሚከተለው የተጨዋቾች ዝውውር ሂደት ከተሳታፊዎች የቀረቡትን ጥያቄዎች የክለቡ የቦርድ አመራር ያለውን ሁኔታ በስፋት የሰጡትን ምላሽ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንቀርብ መሆናችንን ከወዲሁ እንገልፃለን ።