የኢትዮዽያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲቀጥሉ መቂ ከተማ እና ሀምበሪቾ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፋቸውን ከወዲሁ ያረጋገጡበትን ድል አስመዝግበዋል፡፡
08:00 ላይ በተደረገው የምድብ ሀ ጨዋታ መቂ ከተማ ከጨዋታ ብልጫ ጋር የካ ክፍለ ከተማን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
በሁሉም ረገድ ከየካ ተሽለው የቀረቡት መቂ ከተማዎች ጨዋታው በጀመረ 14ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ባሬሳ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ግሩም ጎል አስቆጥሮ መቂን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ። የካዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ተወሰዶባቸው ሳለ እየብ ተሾመ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀይ ካርድ መውጣቱ በየካዎች ላይ የበለጠ ጫና እንዲበዛባቸው አድርጓል። የአንድ ተጨዋች መጉደልን በመጠቀምም መቂዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን አጋጣሚ በኄኖክ ሙሉጌታ እና በኤርምያስ ታደሰ አማካኝነት ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተው የመጀመርያው አጋማሽ በመቂ 1-0 መሪነት እረፍት ተጠናቋል፡፡
ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ ሁኔታ የካዎች ተዳክመው ሲቀርቡ ከእረፍት በየካ ክፍለከተማ በኩል የሚጠቀሰው የጎል ሙከራ ፋአድ ተመስገን ካደረገው ውጭ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ መቂዎች በርከት ያለ የጎል ሙከራ ቢያደርጉም ተጨማሪ ጎል ሳይታከልበት ጨዋታው በመቂ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም መቂ በ4 ነጥቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜ መግባቱን ከወዲሁ አረጋግጧል። በተቃራኒው የካ ክፍለ ከተማ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ በመጨረሻው ጨዋታ መቂ ከተማ ቡታጅራ ከተማን ከ1 የጎል ልዩነት በላይ እንዲያሸነፍ ይጠብቃል፡፡
1. መቂ ከተማ 1 (+1) 3
2. ቡታጅራ ከተማ 1 (0) 1
3. የካ ክፍለከተማ 2 (-1) 1
10:00 ላይ በተደረገው የምድብ ለ ጨዋታ ሀምበሪቾ ደሴ ከተማን 5-2 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል።
የውድድሩ ፈጣን ጎል ከማዕዘን የተሻገረልትን ኳስ በ1ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል አያሌው በማስቆጠር ደሴ ከተማን መሪ ማድረግ ቢችልም ወደ ጨዋታው በሂደት የተመለሱት ሀምበሪቾዎች በፍፁም የበላይነት ከእረፍት በፊት ድንቅነህ ከበደ እና ቢኒያም ጌታቸው ባስቆጠሯቸው ሁለት ግሩም ጎል አማካኝነት ሀምበሪቾን መሪ መሆን ችለዋል። በጉልበት እና ፍጥነት ጠንካራ የነበሩትን የሀምበሪቾዎች እንቅስቃሴ ደሴዎች ፈፅሞ መቋቋም ተስኗቸው የመጀመርያው አጋማሽ በሀምበሪቾ 2-1 መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀምበሪቾዎች ልዩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን ድንቅነህ ከበደ እና ቢንያም ጌታቸው ለራሳቸው ሁለተኛ ለቡድኑ 3ኛ እና 4ኛ ጎል አስቆጥረዋል። ጨዋታው በሀምበሪቾ የበላይነት ቀጥሎ በዕለቱ ጥሩ ሲቀሳቀስ የነበረው ያሬድ አማረ የግብ ጠባቂውን ከግብ ክልሉ መውጣት ተመልክቶ ቺፕ በማድረግ በስታድየሙ የነበረውን ተመልካች ያስጨበጨበ ግሩም ጎል በማስቆጠር የሀምበሪቾን ጎል ወደ አምስት ማድረስ ችሏል፡፡ ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ላይ ሀብቶም ገብሬ ሁለተኛ ጎል ቢያስቆጥርም ደሴ ከተማ ከሽንፈት መታደግ አልቻለም ። ጨዋታውም በሀንበሪቾ 5-2 አሸናፊነት ተጠናቋል ። ውጤቱን ተከትሎ ሀንበሪቾ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፉን አረጋግጧል።
1. ሀምበሪቾ 2 (+3) 4
2. ሚዛን አማን 1 (0) 1
3. ደሴ ከተማ 1 (-3) 0
ውድድሩ ረቡዕ ሲቀጥል ጠዋት 02:00 ቡታጅራ ከተማ ከ መቂ ፤ ረፋድ 04:00 ደግሞሚዛን አማን ከ ከደሴ ከተማ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡