የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) በየሁለት አመቱ የሚያዘጋጀውን የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራት ቁጥር ወደ 24 እንዲያደግ ወስኗል፡፡ የካፍ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ዛሬ በጉዳዬ ዙሪያ ለመመምከር ራባት ላይ ስብሰባ ተቀምጠው ነበር፡፡ በካፍ ሲምፖዚየም ወቅት ከተነሱት ሃሳቦች መካከል አንዱ የሆነው የተሳታፊ ክለቦችን ቁጥር የመጨመር ውሳኔ ዛሬ ፀድቋል፡፡ ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫም ለመጀመሪያ ግዜ በ24 ሃገራት መካከል ይደረጋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ከ1996 ወዲህ በ16 ሃገራት መካከል ሲደረግ የቆየ ሲሆን (በ1996 ናይጄሪያ እሯሷን ከውድድር በማግለሏ ለመጀመሪያ ግዜ 16 ቡድኖች የተካፈሉበት የአፍሪካ ዋንጫ በ1998 ቡርኪናፋሶ ያስተናገደችው ነው፡፡) ከ2019 በኃላ 24 ሃገራት በውድድሩ ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡ ይህም በውድድሩ ለመሳተፍ ቁም ስቅላቸውን ለሚያዩ ሃገራት መልካም ሲሆን አፍሪካ ዋንጫ የነበረው ጣዕምን እና ጥራትን ይበልጥ ያዳክመዋል ለሚሉ የአፍሪካ እግርኳስ አፍቃሪያን መርዶ ነው፡፡
በአህመድ አህመድ የሚመራው ካፍ ከኢሳ ሃያቱ በትረ ስልጣኑን ከተረከበ በኃላ አዳዲን ለውጦችን ለአህጉሪቱ እግርኳስ ማስተዋወቅ እንደሚሰሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የተሳታፊ ሃገራት ቁጥር መጨመር በቴሌቪዥን መብት ሽያጭ እና የስፖንሰር ገቢ እንደሚያሳድገው ካፍ እምነት ሲጥልበት በዛውም ልክ ከአዘጋጅ ሃገር ውድድሩን ለማስተናገድ የመሟላት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችን ይበልጥ እንዲጨምሩ አድርጓል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ በ2019 ካሜሮን የምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ በመካከለኛው አፍሪካዋ ሃገር የመደረጉ ነገር አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ በከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ውድድሩን ለማስተናገድ ጥረት እያደረገች የምትገኘው ካሜሮን በባልስልጣኖቿ በኩል አሁንም ውድድሩን ማስተናገድ እንደምትችል ብትጠቁምም፡፡ የካፍ ሲምፖዚየምን ያስተናገደችው ሞሮኮ እና ግብፅ ከወዲሁ ለአዘጋጅጀነት ሊታጩ ይችላሉ የሚሉ መረጃዎች በስፋት መውጣት ጀምረዋል፡፡