ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ዘማሪያም ወልደጊዮርጊስን የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ወልዲያ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ይታይበት የነበረውን ተጫዋቾች ስብስብ ጥልቀት ችግር ለመቅረፍ በሚመስል መልኩ በዝውውር መስኮቱ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ ይገኛል፡፡ በሁለት ቀናት ልዩነትም አምስት ተጫዋቾችን ማስፈረሙን በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህም መሰረት ግብጠባቂ ስፍራ ላይ የቀድሞው የሰበታ ከተማ ፣ ዳሽን ቢራ እንዲሁም ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታ ያደረገው ደረጀ አለሙን ሲያስፈርሙ በተከላካይ ስፍራ ላይ በሚሌንየሙ መጀመርያ በሊጉ ከፍተኛ ተከፋይ ተጫዋቾች አንዱ የነበረው የቀድሞ የሰበታ ከተማ እና ውሀ ስፖርት የመሀል ተከላካይ ብርሃኔ አንለይን ፣ የመስመር ተከላካዩ ተስፋሁን ሸጋውን ማስፈረም ችለዋል፡፡ በተጨማሪም ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በጅማ አባ ቡና ያሳለፈው ታደለ ምህረቴ እና ቶጓዊው አጥቂ ኤደም ሆሮሶውቪ ሌላች ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ወልዲያ በክረምቱ የዝውውር መስኮት እስካሁን ስምንት ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ሲረጋገጥ ከነዚህም መካከል በአመዛኙ ቡድኑ ያስፈረማቸው የመከላከል ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን መሆናቸው ቡድኑ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ከነበረው የመከላከል ጥንካሬ አንጻር ያልተጠበቀ ሆኗል፡፡