የኢትዮጵያ ክለቦች ሻምፒዮና በዛሬው እለት የ4 ቀን ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ መርሳ ከተማ ወደ ተከታዩ ዙር ማለፋቸውን ያረጋገጡበትን ድል አስመዝግዋል፡፡
ምድብ 1
ትላንት ሊካሄዱ የነበሩት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች የወልዲያ መምህራን ኮሌጅ በዝናብ ምክንያት ማጫወት ባለመቻሉ ዛሬ ንጋት 12:30 ላይ ነበር የተካሄዱት፡፡ መሐመድ አላሙዲ ስታድየም ላይ ወልዲያ የጁ ፍሬ ሽረ እንዳስላሴ ቢ ን 3-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ለየጁ ፍሬ ጀማል ያሲን ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ብሩክ ጌታቸው ቀሪዋን ጎል አስቆጥሯል፡፡
በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ሰአት መልካቆሌ ላይ የተጫወቱት ኢተያ ከተማ እና ያሶ ከተማ ጨዋታቸውን ያለ ግብ አጠናቀዋል፡፡
ምድብ 5
የዚህ ምድብ ጨዋታዎች የተደረጉት በመሐመድ አላሙዲ ስታድየም ሲሆን መርሳ ከተማ ሻሾጎ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ከምድቡ ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፉን ከወዲሁ ማረጋገጥ ችሏል፡፡ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ በተደረገው ጨዋታ ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ አላማጣ ከተማን 2-0 በማሸነፍ ወደ ተከቲዩ ዙር የማለፍ እድሉን ሲያመነምን አላማጣ ከተማ ከምድቡ መሰናበቱን ከወዲሁ አረጋገጧል፡፡ በዚህ ምድብ የመጨረሻ ጨዋታ እኩል የማለፍ እድል የያዙት ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ እና ሻሾጎ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ምድብ 6
በመሐመድ አላሙዲ ስታድየም በተደረጉት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ገንደውሃ ከተማ ሐረር ፖሊስን 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ኦሮሚያ ፖሊስን 2-1 አሸንፏል፡፡
8:00 በጀመረው የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ እና ኦሮሚያ ፖሊስ ጨዋታ የአቃቂ የእንቅስቃሴ ብልጫ የተስተዋለ ሲሆን ኦሮሚያ ፖሊስ በመልሶ ማጥቃት ረዥም ኳስ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።
በ5ኛው ደቂቃ ጉልላት ተሾመ የላከውን ሰንጣቂ ኳስ ፀጋዬ በኃይሉ ወደ ግብነት ቀይሮ አቃቂ ቀዳሚ ሲያደርግ 23ኛው ደቂቃ ድንቅ ብቃቱን ሲያሳይ የነበረው ጉልላት ተሾመ በግራ መስመር ይዞ በመግባት በጥሩ ሁኔታ አቀብሎት ወንድወሰን አስፋው በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሮታል።
ከእረፍት በኋላ ተመጣጣኝ እና ጥሩ የግብ ሙከራዎች ቢስተዋልም ለረዥም ደቂቃ ግብ አልባ ሆኖ ተጉዟል። በመጨረሻም በጭማሪ ደቂቃ ኦሮሚያ ፖሊሶች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት መላኩ ክፍሌ አስቆጥሮ ጨዋታው በአቃቂ ቃሊቲ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቀጥሎ በተካሄደው የገንዳ ውሀ እና ሐረሪ ፖሊስ ጨዋታ ገንዳ ውሃዎች ሙሉ የጨዋታ የበላይነት ነበራቸው፡፡ በ19ኛው ደቂቃ ማንዴላ ደዋስ ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን በጭማሪ ደቂቃ ኤፍሬም ክፍሌ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት በእውቀት አትክልት ወደ ግብነት ቀይሮ በገንዳ ውሃ 2-0 መሪነት ወደ እረፍት አምርተዋል።
ከእረፍት መልስ በ54ኛው ደቂቃ ከወገን ጌታቸው በቀኝ የተላከውን ማንዴላ ደዋስ በቮሊ ማራኪ ግብ አስቆጠሮ የግብ መጠኑን ወደ ሶስት ከፍ ሲያደርገው በ69ኛው ደቂቃ ምንተስኖት ታዘበው የግል ብቃቱን ተጠቅሞ የሀረሪ ፖሊስ ተጫዋቾችን አታሎ አራተኛውን ግብ አስቆጠሯል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ናኦድ ከበደ የሐረሪ ፖሊሶች ትኩረት ማጣትን ተጠቅሞ 5ኛውን ግብ አስቆጥሯል፡፡
በ80ኛው ደቂቃ የሐረሪ ፖሊሱ ብሩክ በላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ ቡድን መሪው ሙሉቀን ዘገየ ቀይ ካርዱን በመቃወም ሜዳ ውስጥ በመግባቱ በተመሳሳይ ከሜዳ እንዲወጣ ተደርጓል። በጭማሪ ደቂቃ ላይ ሐረሪ ፖሊሶች ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት በምንተስኖት ታዘበው አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታው በገንደውሀ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
ምድብ 7
መልካ ቆሌ ላይ በተካሄዱት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ገንፈል ውቅሮ 07 ቀበሌን 3-1 ሲያሸንፍ ጉለሌ ክፍለከተማ ካማሺ ከተማን 3-0 አሸንፏል፡፡ በምድቡ ገንፈል ውቅሮ እና ጉለሌ 4 ነጥብ ሰብስበው ወደ ሁለተኛ ዙር ለማለፍ ተቃርበዋል፡፡
ምድብ 8
መልካቆሌ ላይ የተደረጉት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የአቻ ውጤቶች ተጠናቀዋል፡፡ 08:00 ላይ ሺንሸቾ ከተማ ከ ጫንጮ ከተማ 1-1 ሲለያዩ 10:00 ላይ አቃቂ ማዞርያ ከ06 ቀበሌ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡
ውድድሩ ነገም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህን ሊንክ ተጭነው ሙሉውን መርሀ ግብር ፣ ውጤት እና ሰንጠረዥ ያገኛሉ፡– የክልል ክለቦች ሻምፒዮና