የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በወልዲያ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴም በሀሰተኛ ማስረጃ ተጫዋቾችን በማሰለፍ ውጤት ያለ አግባብ አግኝቷል ያለው አረካ ከተማ እግርኳስ ክለብ ፣ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኝ እና የቡድን መሪ ላይ ቅጣቱን አስተላልፏል፡፡
በምድብ 4 ተደልድሎ ጨዋታውን ሲያደርግ የነበረውና በ7 ነጥብ ወደ 2ኛ ዙር በአንደኝነት ማለፍ የቻለው አረካ ከተማ 7 ተጫዋቾችን ስማቸውን ቀይሮ መታወቂያ በማዘጋጀት በውድድሩ ላይ ተመዝግበው እንዲጫወቱ ማድረጉ በመረጋገጡ ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች ያስመዘገበው ውጤት ተሰርዞ ለተጋጣሚዎቻቸው ፎርፌ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡
ስማቸውን በመቀየር ለአረካ ከተማ እንዲሰለፉ የተደረጉ ተጫዋቾች ዝርዝር
ትክክለኛ ስም – ክለብ – በአረካ የተጫወቱበት ስም
1 ጥበቡ ከበደ – መከላከያ (U20) – ትርኢት ከበደ
2 ሐብተአብ አለሙ – ሀዲያ ሌሙ – መሰረት ዓለሙ
3 አማኑኤል ተስፋዬ – ወላይታ ድቻ (U20) – ቡሲ ተስፋዬ
4 ዓንዱአለም አየለ – ወላይታ ሶዶ – እንዳልካቸው ህዝቅኤል
5 ዘላለም በየነ – መከላከያ (U20) – በቀለ ጃሬ
6 ምናሉ ገለቱ – ወላይታ ድቻ (U20) – አበበ ኢያሱ
7 ዘርአይ ዘነበ – ሀዲያ ሌሙ – ሰራዊት ገረሱ
ከላይ ከተጠቀሱት 7 ተጫዋቾች መካከል ከዘርአይ ዘነበ በቀር ሌሎቹ ስድስት ተጫዋቾች ለፈፀሙት የማታለል ተግባር እያንዳንዳቸው 5ሺህ ብር ቅጣት እና ለ6 ወራት ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ እንዲታገዱ ወስኗል፡፡ ዘርአይ ዘነበ ላይ ደግሞ ተጨማሪ የማጣራት ስራ ተከናውኖ የቅጣት ውሳኔ እንደሚተላለፍበት ታውቋል፡፡
የክለቡ አሰልጣኝ ፋሲካ ጡናሞ ስማቸው መቀየሩን እያወቁ ሆን ብለው እንዲጫወቱ አድርገዋል በሚል 10ሺህ ብር እና ለ1 አመት ከማንኛውም የእግርኳስ ስራዎች ታግደዋል፡፡ የቡድን መሪው አቶ ታሪኮ ማዴቦም በተመሳሳይ የአንድ አመት እገዳ ተላልፎባቸዋል፡፡
አረካ ከተማ በማታለል ተግባሩ ምክንያት የተጫወታቸው 3 ጨዋታዎች ለተጋጣሚዎቹ ፎርፌ እንዲሰጥ ከመወሰኑ በተጨማሪ የ60 ሺህ ብር ቅጣት ተላልፎበታል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም ሰንዳፋ በኬ በ7 ነጥቦች (ብዙ ባስቆጠረ) በቀዳሚነት ፣ ነስር ክለብ በ7 ነጥቦች በሁለተኝነት ከምድባቸው ማለፍ ችለዋል፡፡