የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሰኞ እለት ወደ ሀዋሳ በማምራት እሁድ ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ በ19 ተጫዋቾች ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኝ ሲሆን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም ለአንድ ተጫዋች ጥሪ አድርገዋል፡፡
በትላንትናው የቡድኑ የልምምድ መርሀ ግብር ላይ ከዚሀ ቀደም በጉዳት ከቡድኑ ውጪ ሆኖ የነበረውና በድጋሚ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ የቀረበለት ታደለ መንገሻ መጠነኛ ጉዳት ያጋጠመው ቢሆንም አገግሞ በዛሬው እለት ልምምዱን ሰርቷል፡፡ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም የታደለ መንገሻን ምትክ ሊሆን የሚችል ለማዘጋጀት በሚመስል መልኩ የሀዋሳ ከተማው ፍሬው ሰለሞንን በቡድናቸው ውስጥ አካተውታል፡፡ በዛሬው እለት ረፋድ ልምምድ ላይም ከቡድኑ ጋር የመጀመርያ ልምምዱን አከናውናሏል፡፡
የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ረፋድ 05:00 ላይ ሀዋሳ የደረሰ ሲሆን በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴልም መቀመጫውን አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ እና የሱዳን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ በመጪው እሁድ በሀዋሳ ኢንርናሽናል ስታድየም 10:00 ላይ ይደረጋል፡፡ የመልሱ ጨዋታ ከሳምንት በኋላ ሱዳን ላይ ከተካሄደ በኋላም በድምር ውጤት የሚያሸንፈው ቡድን በጃንዋሪ 2018 ኬንያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የሚያልፍ ይሆናል፡፡