ሁለት ክለቦችን ሲያወዛግብ የነበረው የክሪዚስቶም ንታምቢ ጉዳይ በመጨረሻም ውሳኔ አግኝቷል።
ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማን ሲያወዛግብ የነበረው የአማካይ መስመር ተጨዋቹ ክሪዚስቶም ንታምቢ በመጨረሻም ተገቢነቱ ለኢትዮጵያ ቡና መሆኑ ተረጋግጧል። የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ክሪዚስቶም ንታምቢን ወደ ክለቡ ለመቀላቀል እንደተስማሙ እና ተጨዋቹን የግላቸው ለማድረግ በይፋ ለመስፈረም እንቅስቃሴ ላይ እንደነበሩ ሲዘገብ ቆይቷል። ሆኖም ተጨዋቹ የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከመከፈቱ በፊት ለአዳማ ከተማ ህጋዊ ባልሆነ መልኩ በመፈረሙ ተቀባይነት እንደማያገኝ በመግለፅ ተጨዋቹን በህጋዊ መልኩ የቪዛ እና የትራንስፖርት ወጪውን በመሸፈን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣታቸው እንዲሁም ሃምሌ 25 የሚከፈተውን የውጪ ሃገር የተጨዋቾችን የዝውውር መስኮት በመጠቀም ከተጫዋቹ ጋር በመስማማታቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ተጨዋቹ ለኢትዮጵያ ቡና መሆኑ አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ቡናዎች ከዚህ በፊት ቶማስ ስምረቱን ወንድወሸን አሸናፊ ፣ አለማየሁ ሙለታ ፣ ሮቤል አስራት ፣ አብዱልሰላም አማን ፣ አስራት ቱንጆ ፣ ድንቅነህ ከበደ ፣ በረከት አድማሱ እና ትግስቱ አበራን ያስፈረሙ ሲሆን በቀጣይ ክሪዚስቶም ንታምቢ 9ኛ ፈራሚ ሆኖ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ይጠበቃል፡፡