በነገው ጨዋታ ዙርያ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የሆኑት ጌታነህ ከበደ ፣ አስቻለው ታመነ እና ጀማል ጣሰው አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡
ጌታነህ ከበደ
ስለ ዝግጅታቸው
ዝግጅታችን ጥሩ ነው፡፡ ሀዋሳ ከመጣን አንድ ሳምንት አስቆጥረናል፡፡ ከጅቡቲ ጫዋታ ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል እየተዘጋጀን ቆይተናል፡፡ በተወሰነ ጊዜም ቢሆን በሚገባ ተዘጋጅተናል፡፡
የወዳጅነት ጨዋታው (ከዛምቢያ ጋር የተደረገው) ለነገው ጨዋታ የሚሰጠው ጠቀሜታ
የወዳጅነት ጨዋታውን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው ብዬ መግለፅ እችላለው፡፡ የጋና ጨዋታም ደረጃችንን ዝቅ አድርጎትና ተጽእኖ ፈጥሮብን ነበር፡፡ የዛምቢያውን ጨዋታ ማድረጋችንም ያን ክፍተት በሚገባ ያሳየን ነው፡፡
ስለ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን
የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል የተወሰኑ ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ በአጠቃላይ ቡድናቸው እንደ አዲስ ነው የተዋቀረው፡፡ ስለ ተጋጣሚያችን ብዙም ባናውቅም አሰልጣኛችን ለነሱ የሚሆን ዝግጅት እንድንዘጋጅ አድርጎናል፡፡
ጨዋታው በርግጠኝነት ይከብዳል፡፡ ሆኖም ያኔ (2013) እኛ አሸንፈናቸው ለአፍሪካ ዋንጫ እንዳለፍነው ሁሉ አሁን ላይም ከነሱ የተሻለ አቅም ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡
ጅቡቲ ላይ 4 ግቦችን ማስቆጠር
ለሀገር ስትጫወት ሁልግዜም ጎል ማስቆጠር ይኖርብሀል፡፡ እንደ አጥቂም ስታስበው ጎል ማግባት አለብህ፡፡ ግብ ስታስቆጥር ተነሳሽነትን ይጨምርልሀል ፤ ጅቡቲ ላዬ ማስቆጠሬም ለኔ ትልቅ ወኔ ሰጥቶኛል፡፡
ስለ ደጋፊዎች
የመልሱ ጨዋታ ከሜዳችን ውጪ ስለሚሆን እዚሁ ጨርሰን ለመሄድ ነው የምንፈልገው፡፡ ደጋፊው ከጎናችን ነው፡፡ ባህር ዳርም ፣ ሀዋሳም ፣ አዲስ አበባም ጥሩ ነገር በደጋፊዎቻችን ላይ አለ፡፡ ራሱ ደጋፊው ስለሚያውቀውም ብዙም መናገር አልፈልግም፡፡
አስቻለው ታመነ
ዝግጅት
የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ በሚገባ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ሁላችንም ጨዋታውን እዚሁ መጨረሰን አስበናል፡፡ በጥሩ ዝግጅት እንደመስራታችን ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፡፡
ስለ ወዳጅነት ጨዋታው
የወዳጅነት ጨዋታ ማድረጋችን ጠቃሚ እና አቅማችንን የተመለከትንበት ሆኗል፡፡ ዛምቢያ ትልቅ ቡድን በመሆኑ እኛ አቅማችንን አይተናል፡፡ ምንም እንኳን ወዳጅነት ቢሆንም ጥሩ ነገር ይዘንበት መጥተናል፡፡
ስለጨዋታው
በርግጠኝነት እናሸንፋለን፡፡ ጨዋታው በሜዳችን እንደመሆኑ ማሸነፍ አለብን፡፡ እዚሁ ጨርሰን ለመውጣት እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብዬ አስባለው፡፡
ስለ ደጋፊው
ሀገርን ወክለን እንደመጫወታችን መጠን ደጋፊው ስታድየም በመገኘት ዘጠናውን ደቂቃ ቢደግፈን የሚል መልዕክት አለኝ፡፡
ጀማል ጣሰው
ዝግጅት
ቡድኑ ላይ በጣም ጥሩ ስሜት ነው ያለው፡፡ ይህ ቡድን አዲስ ነው ፤ ሁሉም ነገሩ አዲስ የሆነ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ በዚህ ቡድን እንደመቆየቴ አሁን ያለው በአዳዲስ ተጫዋቾች የተሞላ ነገር አያለው ፤ ጥሩ ነገርም አላቸው፡፡ ነገም አብረን እናየዋለን፡፡
ስለ ሱዳን ብሔራዊ ቡድን
የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጠንካራ ቡድን ነበራቸው፡፡ ያኔ በ 2013 ማጣሪያ ላይ ተገናኝተን ነበር፡፡ ከዛ በኃላ አልተገናኘንም፡፡ ሆኖም ቡድናቸው ጥሩ መሆኑን ነው ማውቀው፡፡ እኛም ሀገራችን ላይ የሚገባውን ሁሉ አድርገን ጨዋታውን እዚሁ ጨርሰን መውጣት አለብን፡፡
ስለ ደጋፊዎች
ጨዋታው የሀገር መሆኑ የሚታወቀው ደጋፊ ሲኖር ነው፡፡ ከደጋፊው ትልቅ ነገር ይጠበቃል ፤ ምንም ነገር ይምጣ ጨዋታውን እዚሁ ጨርሰን ነው ወደ ቀጣይ መሄድ ያለብን፡፡ ይህም ማለት ኳሱ የሚፈቅደውን አድርገን በደጋፊያችን ብርታት አሸንፈን ማለፍ አለብን የሚል ስሜት አለኝ፡፡ ማሸነፍ የመጨረሻ መልዕክቴ ናት፡፡