በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮና (ቻን) ማጣርያ እሁድ እለት ሀዋሳ ላይ ሱዳንን ገጥሞ 1-1 የተለያየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ነገ ወደ ሱዳን ኦቤይድ ያመራል፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለጨዋታው ተጨማሪ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ እንደማይቀላቅሉ የገለፁ ሲሆን ትናንት እና ዛሬ ከሰአት 9፡00 ላይ በሀዋሳ የሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ልምምዳቸውን ሰርተዋል፡፡ ነገ ማለዳ 12፡00 ላይም የመጨረሻ ልምምዳቸውን እንደሚሰሩና ረፋድ ላይ ከሀዋሳ ተነስተው በአዲስ አበባ በኩል በማድረግ ወደ ሱዳን የሚጓዙ ይሆናል፡፡ በሀዋሳው ጨዋታ በፓስፖርት አለመታደስ ምክንያት 18 ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ ሳይካተት የቀረው ፍሬው ሰለሞን የፓስፖርት ጉዳዩ ተጠናቆ ወደ ስፍራው እንደሚያመራም ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን አርብ ምሽት የሚያደርግ ሲሆን ወደ ኬንያው ውድድር ለማለፍ ማሸነፍ አልያም ከአንድ ግብ በላይ አስቆጥሮ አቻ መለያየት ይጠበቅበታል፡፡