በአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) የመጨረሻ ማጣርያ የመልሰ ጨዋታ ወደ ሱዳን ኦቤይድ ያቀናው የኢትዮጵያ ብሔራወ ቡድን 1-0 ተሸንፎ በድምር ውጤት ከውድድሩ ውጪ ሆኗል፡፡
አሰልጣኘ አሸናፊ በቀለ ሀዋሳ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ እጅግ ደካማ ከሆነ እንቅስቃሴ ጋር 1-1 ከተለያየው ቡድናቸው የመጀመርያ አሰላለፍ ላይ በአማካይ ስፍራ ፍሬው ሰለሞንን በታፈሰ ሰለሞን በመተካት ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡
የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት የመጀመርያው አጋማሽ የሚቆራረጡ ቅብብሎች እና አሰልቺ እንቅስቃሴዎች ተስተውሎበታል፡፡ ሱዳኖች በአንፃራዊነት የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም የሚጠቀስ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው በመጫወት የጀመሩት ሱዳኖች ኳስና መረብን ለማገናኘት ሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበሩ ያስፈለጓቸው። ይህችም ጎል 47ኛው ደቂቃ ላይ በኤልሳምኒ ኤልሳዊ አማካይነት የተገኘች ነበረች። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች መሀል ለመሀል በነበረው ክፍተት በመጠቀም የተሰነጠቀለትን ኳስ በሳጥን ውስጥ ይገኝ የነበረው ኤልሳምኒ ለማቆም ሲሞክር ወደላይ ቢነሳበትም ኳሷ ወደ መሬት ስትመለስ አየር ላይ እንዳለች በአክሮባቲክ ምት በመምታት በጀማል ጣሰው አናት ላይ የጨዋታውን ብቸኛ ጎል በአስደናቂ አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ በኃላም ሱዳኖች በጫናቸው የገፉበት ሲሆን በ52 እና 58ኛው ደቂቃዎች ላይ በመአዝ አብዱልርሀማን አማካይነት ያደረጓቸው ሙከራዎች በግቡ አናት ወጡ እንጂ መሪነታቸውን ለማስፋት ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩ ።
ዋልያዎቹ የተጋጣሚያቸውን ጥቃት ለመከላከል ሲሞክሩ ቢቆዩም ወደፊት ገፍተው ለማጥቃት ግን ፍፁም ተቸግረው ታይተዋል ። በተለይም ቡድኑ አልፎ አልፎ ሚያገኛቸውን ክፍተቶች ለመጠቀም የሚያደርገው ጥረት በተጨዋቾች መሀል ሲታዩ በነበሩ ቁጥራቸው በተበራከቱ ያልተሳኩ ቅብብሎች ምክንያት ከጅምሩ ሲደናቀፍ መታዘብ ችለናል። ከተከላካይ መስመር በቀጥታ ወደፊት ይላኩ የነበሩ ረጃጅም ኳሶችም በቀላሉ በሱዳን ተከላካዮች ቁጥጥር ስር ከመውደቅ ውጪ ይህ ነው የሚባል አደጋ መፍጠር አልቻሉም።
ምንአልባትም ሱዳኖች ውጤት ለማስጠበቅ ከ65ኛው ደቂቃ በኃላ በመጠኑ ወደራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው መጫወት መጀመራቸው ዋልያዎቹ የተሻለ የኳስ ቅብብል ሂደት እንዲኖራቸው ዕድል ቢፈጥርላቸውም ወደሱዳኖች የግብ ክልል ድረስ ዘልቆ የሚገባ የማጥቃት እንቅስቃሴ ግን ማድረግ አልቻሉም። 67ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ጠርዝ ላይ ሞክሮ በግቡ አናት መረቡን ታኮ ከወጣበት ሙከራ ውጪ ቡድኑ ሌላ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ነበር ጨዋታውን የጨረሰው። በተቃራኒው በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የነበሩት ሱዳኖች 82ኛው ደቂቃ ላይ በዋልየልዲን ከድር ከሳጥኑ አቅርቢያ ጥሩ ሙከራ አርገው የነበረ ቢሆንም ጀማል ጣሰው ለጥቂት አድኖባቸዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይም እምብዛም የሚያስጨንቅ የጨዋታ እንቅስቃሴ ከተጋጣሚያቸው ያልገጠማቸው ሱዳኖች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ግብ ሳያስተናግዱ በመዝለቅ ባለድል መሆን ችለዋል። በዚህም መሰረት ሱዳን ኢትዮጵያን በ2-1 የድምር ውጤት በመርታት በጥር ወር ኬንያ ላይ ለሚስተናገደው የ2018ቱ የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮና (ቻን ) ማለፏን አረጋግጣለች ።
በ2014 በደቡብ አፍሪካ ፣ በ2016 በሩዋንዳ የተስተናገዱት ውድሮች ላይ የተካፈለችው ኢትዮጵያ ከሶስተኛ ተከታታይ ውድድር ስትቀር ሱዳን በ2011 ራሷ ካስተናገደችው ውድድር በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ውድድሩ የምታመራ ይሆናል፡፡