በየዓመቱ ክረምት መግቢያ በሀዋሳ ከተማ በተለምዶ ቄራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚደረገው እና ዘንድሮም በ02 ቄራ ሜዳ ላይ በርካታ ቡድኖችን እያሳተፈ የቆየው የእግር ኳስ ሻምፒዮና እሁድ ተጠናቋል፡፡
ለ23ኛ ጊዜ የተካሄደው ይህ የእግር ኳስ ውደድር በአከባቢው ባሉ ወጣቶች የሚዘጋጅ ሲሆን በርካታ ትልልቅ ተጫዋቾችም ከዚህ ውድድር ተገኝተዋል፡፡ እንደ ሲሳይ ባንጫ፣ ተስፋዬ በቀለ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ፍሬው ሰለሞን፣ ዘነበ ከበደ፣ አሁን ለጀርመኑ ኤስቪጂ ኢለበን የሚጫወተው አማኑኤል ባሻዬ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሌሎች በርካታ የወንድ እና የሴት ተጫዋቾችም ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡
በየአመቱ የሚካሄደው ይህ የቄራ ሀዋሳ ዋንጫ ዘንድሮም ካሳለፍነው ሐምሌ 1 ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ እሁድ ነሀሴ 14 ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ ይህ ውድድር በሊጉ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ስም የተሰየሙ ቡድኖችን ጨምሮ በ32 ቡድኖች መካከል የተደረገ ሲሆን በፍፃሜው መታፈሪያ ኮንስትራክሽን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ጋር ጨዋታቸውን አድርገው ያለምንም ግብ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በመጠናቀቁ በተሰጠው የመለያ ምት ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ ቡድኑን ለማበረታታት ከአዲስ አበባ ተጉዘው የመጡት በርካታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም በሜዳው በመገኘት ድጋፋቸውን ሲሰጡ እና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ ተመልክተናል፡፡
በውድድሩ ላይ ኮከብ አሰልጣኞች ፣ ተጫዋቾች እንዲሁም በበርካታ ዘርፎች ሽልማቶች የተበረከቱ ሲሆን በቀጣይም ውድድሩን ሀገራዊ ለማድረግ እና ሜዳው ያለበትን የቦታ ጥበት ወሰን ለማስከበር እንደሚሰራ የቄራ ወጣቶች አስተባባሪ አቶ አበራ ደገፉ ተናግረዋል፡፡
በዚህ አመታዊ የወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር ከእግር ኳስ ውድድርነቱ ባለፈ በርካታ የክለብ አሰልጣኞች በመገኘት ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ተጫዋቾችን ለመምረጥ ሰፊ እድልን የፈጠረ አጋጣሚ ሆኗል፡፡ መከላከያ ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሀምበሪቾ ከተማ፣ ሻሸመኔ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ሌሎች ክለቦችም በድምሩ 33 ተጫዋቾችን ከዘንድሮው ውድድር ብቻ ለ20 እና 17 አመት በታች እንዲሁም ዋናው ቡድናቸው መመልመል ችለዋል፡፡
የቄራ ዋንጫ ውድድር ላይ አግራምትን ከሚያጭሩት ነገሮች መካከል ሜዳው ምንም እንኳን ለተመልካቾች ምቹ የሆነ የመቀመጫ ስፍራ ባይኖረውም እያንዳንዱ ተመልካች ከቤቱ በሚያመጣው ወንበር ተቀምጦ ጨዋታዎችን ሲከታተል ማየት የተለመደ ነው፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ ውድድሩን ለበርካታ ጊዜያት ከታደሙ ተመልካቾች ባገኘችው መረጃ መሰረት ከ90 በላይ በሀገራችን ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ያፈራው ይህ ውድድር ሊበረታታ የሚበገባው በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረት እና ድጋፍ ቢያደርጉለት የበለጠ ውጤታማ መሆን የሚችል ውድድር ነው፡፡