አርባምንጭ ከተማ ናይጄሪያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ላኪ ሰኒን በእጁ አሰገብቷል፡፡
ከሲዳማ ቡና ለአንድ አመት ለመጫወት ተጨማሪ ኮንትራት ቀርቦለት መስማማቱ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም አርባምንጭ ከተማ በህጋዊ መንገድ የግሉ ማድረጉን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
ላኪ ሰኒ ወደ ኢትዮጽያ በመምጣት ለጅማ አባቡና እና ሲዳማ ቡና ያለፉትን 4 አመታት የተጫወተ ሲሆን አመለ ሚልኪያስን በለቀቀው አርባምጭ የአጥቂ መስመር ክፍተቱን ይደፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዝውውሩ ላኪ ሳኒን በአርባምንጭ ከተማ ታሪክ ሁለተኛው የውጭ ዜጋ ሲያደርገው ከሲሳይ ባንጫ ፣ ዮናታን ከበደ ፣ ታዲዮስ ወልዴ እና ጋናዊውን ሰይዱ ባንሴ በመቀጠል 5ኛው የክለቡ ፈራሚ ሆኗል፡፡
አርባምንጭ ከተማ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ አጥቂው ገብረሚካኤል ያዕቆብ እና ተከላካዩ ታገል አበበን የአንድ አመት ተጨማሪ ኮንትራት የሰጠ ሲሆን ከተስፋ ቡድን ያደጉት ግብ ጠባቂው ጽዮን መርዕድ ና አስጨናቂ ፀጋዬን ውልም ለሁለት አመት ማራዘሙን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌሌ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡