ፋሲል ከተማዎች ዛሬ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፃቸው በዝውውር መስኮቱ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ የነበረውን አይናለም ኃይሉንም ማስፈረማቸውን አስታውቀዋል፡፡ አፄዎቹ ከአይናለም በተጨማሪ የድሬዳዋ ከተማውን ግብ ጠባቂ ቢኒያም ሃብታሙን የግላቸው ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
አይናለም በ2006 የውድድር አመት የወቅቱ የሀገሪቱ ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን ዳሽን ቢራን ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን ከዳሽን በኋላ ሁለት የውድድር ዘመናትን ወደ ደደቢት ተመልሶ አሳልፎ አሁን ደግሞ ወደ ጎንደር በድጋሚ በመመለስ ለፋሲል ፊርማውን ማኖር ችሏል፡፡
ሌላው የክለቡ ፈራሚ ቢንያም ሐብታሙ በድሬዳዋ ከተማ የሳመሶን አሰፋ ተጠባባቂ በመሆን የውድድር አመቱን ያሳለፈ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላ በድጋሚ ወደ ጎንደር በመመለስ የፋሲል ከተማ ንብረት ሆኗል፡፡ ከዚህ ፊርማ ጋር በተያያዘም አፄዎቹ ከዚህ ቀደም ካስፈረሙት ሌላው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን ጋር መለያየታቸው ታውቋል፡፡
የጎንደሩ ክለብ ከዚህ በፊት ስድስት የሃገር ውስጥ ተጨዋቾችን ማስፈረም የቻለ ሲሆን ከሃገር ውጪም ሶስት ተጨዋቾችን በማምጣት የሙከራ ጊዜ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡ የዩጋንዳ ዜግነት ያለውና ከዚህ ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ አጭር ጊዜ ያሳለፈው ሮበርት ሴንቴንጎ ፋሲሎችን ለሙከራ መቀላቀሉ ሲገለፅ ሚካኤል ሳማኪ የተባለ ግብ ጠባቂ እና ክርስቶፈር አምሶቢ የተባለ ተጨዋችንም ሌሎቹ የሙከራ እድል የተሰጣቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡