በካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ቅዳሜ ምሽት በተደረጉ ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ ቲፒ ማዜምቤ፣ ኤምሲ አልጀር እና ፉስ ራባት ማሸነፍ ችለዋል፡፡ የአምናው የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ባለድል ቲፒ ማዜምቤ ከሜዳው ውጪ አል ሂላል ኦባያድን ሲረታ ፉስ ራባት ሴፋክሲየንን እንዲሁም ኤምሲ አልጀር ክለብ አፍሪካ በተመሳሳይ 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ቲፒ ማዜምቤ ዳግም የኮንፌድሬሽን ዋንጫ አሸናፊ ለመሆን የሚያደርገውን ጉዞ ያሳመረበትን ድል አል ሂላል ኦባያድን በማሸነፍ አሳምሯል፡፡ 2-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ አል ሂላል አባያዶች የማዜምቤው ኬቨን ሞንዴኮ በራሱ ግብ ላይ ባስቆጠረው ግብ በ23ኛው ደቂቃ መሪ ቢሆኑም ንጊታ ማላንጎ ከ7 ደቂቃዎች በኃላ ማዜምቤን አቻ አድርጓል፡፡ ከእረፍት መልስ ማላንጎ በፍፁም ቅጣት ምት የሉቡምባሺውን ክለብ ለድል ያበቃች ድል አስመዝግቧል፡፡
ፉስ ራባት በካሪም ቤንአሪፍ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ሴፋክሲየንን 1-0 ሲረታ ኤምሲ አልጀር በበኩሉ በሃኪም ነካች የ8ተኛ ደቂቃ ደቂቃ ግብ ክለብ አፍሪካን ማሸነፍ ችሏል፡፡ የመልስ ጨዋታዎች በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረጉ ሲሆን ዜስኮ ዩናይትድ እና ቲፒ ማዜምቤ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ከፍተኛ እድል አላቸው፡፡ በሰሜን አፍሪካ ደርቢ የተመዘገቡት ውጤቶች ግን አላፊውን ቡድን ለመገመት አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡
ውጤቶች
ሱፐርስፖርት ዩናትድ 0-0 ዜስኮ ዩናይትድ
አል ሂላል ኦባያድ 1-2 ቲፒ ማዜምቤ
ፋት ዩኒየን ስፖርት 1-0 ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን
ሞሊዲያ ክለብ ደ አልጀር 1-0 ክለብ አፍሪካ