የቅዱስ ስፖርት ማህበር በየአመቱ መስከረም ወር ላይ የሚያካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ፣ የቦርድ አመራሮች ፣ የፅህፈት ቤት ሰራተኞች ፣ በርከት ያሉ የክለቡ የተመዘገቡ ደጋፊዎችን ጨምሮ 1461 አባላት በተገኙበት በአዲስ አበባ በሚሌንየም አዳራሽ የክለቡ አባላት በታደሙበት ተካሄደ፡፡
ምልዐተ ጉባኤው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኋላ በዕለቱ የተያዙት አጀንዳዎች እንደ ቅድመ ተከተላቸው ለጉባኤው የቀረቡ ሲሆን በቀዳሚነት የማህበሩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል አማካኝነት የ2009 የስራ ሪፖርት በዝርዝር ቀርቧል።
በሪፖርቱ በዋናነት ከተነሱት የክለቡ ስኬቶች መካከል
* የክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ተገንብቶ መመረቁ፡፡
* በ2009 የውድድር አመት የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ መሆን እና በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እስከ ምድብ ድልድል መድረሱ፡፡
* ደጋፊው ከመቼው ጊዜ በላይ በስፖርታዊ ጨዋነት ያሳዩት በጎ ተግባር፡፡
* ክለቡ በተሳተፈባቸው የውድድር መድረኮች ከትኬት ሽያጭ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱ
* በማህበራዊ ተሳትፎው ክለቡ ከደጋፊዎቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን መወጣቱ እና ሌሎች የስኬት አመት ማሳለፋቸውን በዝርዝር ገልፀዋል፡፡
አቶ አብነት በሪፖርታቸው በ2009 መስራት እየተገባቸው ያላከናወናቸው ድክመቶች ብለው ካቀረቧቸው መካከል፡-
-የክለቡ የስታድየም ግንባታ ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ አለመጀመሩ
-ክለቡ እንደተሳተፈበት የውድድር ብዛት እና ትልቅ መድረክ ተጨማሪ ድርጅቶችን ወደ ክለቡ ጋብዞ የክለቡን አቅም አለማሳደግ የተጠቀሱ ናቸው፡፡
በቀጣይ ጊዜያት ክለቡ እንደ ስጋት ያቀረባቸው ነጥቦች የሀገሪቱ የስፖርት ፖሊሲ አቀራረፅ ለክለቦች እድገት እንቅፋት መሆኑ ፣ የፌዴሬሽን የተጨዋቾች የዝውውር ህግ ከአለም አቀፍ የተጨዋቾች ዝውውር ህግ ጋር የማይጣጣም መሆኑ ፣ የኢትዮዽያ እግር ኳስ አደረጃጀት ዘመናዊ እና አለማቀፋዊ አለመሆኑ ናቸው ።
በመቀጠል የስፖርት ማህበሩ የ2009 የፈይናስ ኦዲት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱም ምንም ጥያቄ ሳይቀርብበት በምላተ ጉባኤው ሙሉ ድምፅ የፋይናስ ሪፖርቱን አፅድቋል ።
ጉባኤው በማስከተል በ2009 በቀረበው ሪፖርት ዙርያ በጉባኤው ተሳታፊዎች በርከት ያሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን አቶ አብነት ገብረመስቀል ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ተጨዋቾች የሚመጡበት ሒደት መስተካከል እንዳለበት እና ለዚህም ቦርዱ በምልመላው ላይ ከአሰልጣኞቹ ባሻገር ራሱ እንደገባበት ተናግረው የደጋፊው እና የክለቡ ተጨዋቾች የሚለብሱት ማልያ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ የስታድየም ግንባታን በተመለከተ በልዩ ሁኔታ እንደሚያዩት ገልፀው የተሰጡትን አስተያየቶች እንደ ግብአት ወስደው ወደ መፍትሄ እንደሚመጡ አሳውቀዋል፡፡ ጉባኤውም በአብላጫ ድምፅ የ2009 የሪፖርት አፈፃፀምን አፅድቋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር የ2010 በጀት ዓመት የሦራ ዕቅድ በአቶ ነዋይ በየነ አማካኝነት በዝርዝር ቀርቧል፡፡ አቶ ንዋይ በእቅድ ገለጻቸው በዋናነት የንግድ ድርጅት ማቋቋም ፣ የስፖርት ማህበሩን መተዳደርያ ማሻሻል ፣ አዳዲስ ከፍተኛ ስፖንሰሮችን ማፈላለግ እና ሌሎች ሀሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን በጉባኤው ታዳሚዎች ጥያቄ ከጉባኤው መሪዎች ምላሽ ተሰጥቶ በሙሉ ድምፅ የ2010 አመት በጀትን አፅድቀዋል።
በ2009 በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የእግድ ውሳኔ የተላለፈባቸው አቶ ተስፋዬ ነጋሽ ፣ አቶ ዳንኤል ካሳ ፣ አቶ አንተነህ ፈለቀ ፣ አቶ ታደሰ መሸሻ ፣ አቶ ዮሴፍ አለማየሁ በተመለከተ ለጉባዬው በቀረበው የውይይት አጀንዳ ላይ በሁለት ጎራ የተከፈለ ልዩነት የታየ ሲሆን አቶ ዮሴፍ አለማየሁ ይቅርታ መጠየቃቸውን ተከትሎ እግዱ ሲነሳላቸው የተቀሩት አራቱ አባላት ጉባኤ አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ የክለቡን ጥቅምና ህልውና አሳልፈው ሰጥተዋል በሚልም ከ1461 አባላት ውስጥ በ58 ተቃውሞ ፣ በ57 ድምፀ ተአቅቦ እና በ1325 ድጋፍ በድምፅ ብልጫ አንተነህ ፈለቀ ፣ ዳንኤል ካሳ ፣ ታደሰ መሻሻ ፣ ተስፋዬ ነጋሽ ከአባልነት ሙሉ ለሙሉ በጉባኤው ውሳኔ ተሰርዘዋል ።
ክለቡ አቶ አብነት ገብረ መስቀል በልዩ ሁኔታ እንደሚናገሩ በገለፁት መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ወደ አክሲዮን እንዲሸጋገር በማሰብ ለውይይት የቀረበ መነሻ ሰነድ ይፋ አድርገዋል። ከደጋፊዎቹም ክለቡ ወደ አክስዮን መሻገሩ የክለብ ባለቤትነታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ሲያስቀምጡ ሲሆን ከመድረኩም ይህ መነሻ ሀሳብ እንደሆነ እና ወደፊት በሬዲዮ ፣ በልሳነ ጊዮርጊስ ጋዜጣ እንዲሁም ከደጋፊዎች ጋር በሚደረጉ ሰፋ ያሉ የውይይት መድረኮች ሀሳብ አስተያየት ከተሰጠባቸው በኃላ ለውሳኔ እንደሚቀርብ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ጁነይዲ ባሻ የመዝግያ መልክት አቅርበው የጠቅላላው ጉባኤ ፍፃሜ ሆኗል።
ከጉባኤው መጠናቀቀቅ በኋላ የክለቡ ፕሬዝደንት አቶ አብነት ገብረ መስቀል እና የቦርድ አመራር ከጠቅላላ ጉባኤው እና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ መሆኑን ከወዲሁ እናሳውቃን።