የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የምድብ ለ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም (ሰው ሰራሽ ሳር) ተካሂደው ድሬዳዋ ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ ያለምንም ግብ ሲያጠናቅቁ ሲዳማ ቡና ወልዲያን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ 0-0 አርባምንጭ ከተማ
08:20 ላይ የተጀመረው ይህ ጨዋታ ሙሉውን ክፍለ ጊዜ ይህ ነው የሚባል ወጥ እንቅስቃሴን ያልተመለከትንበት ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ድሬዳዋዎች አልፎ አልፎ ወደ ግብ በመድረስ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ ሆኖ ታይተዋል፡፡ በተለይም አህመድ ረሺድ እና ዘነበ ከበደ ከመስመር እየሰበሩ በመግባት የሚያደርጉት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ በአርባምንጭ ከተማ በኩል በ31ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ዮናታን ከበደ ሞክሮ ሳምሶን አሰፋ ካወጣት ኳስ ውጭ ተጨማሪ ሙከራን ሳያደርጉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እድሎችን በመፍጠር ድሬዳዋዎች አሁንም የተሻሉ ሆነው ታይተዋል፡፡ አህመድ ረሺድ ከቀኝ መስመር አቀብሎት ዘላለም ኢሳያስ ያደረጋት ሙከራ ፤ በአርባምንጭ በኩል ደግሞ ታዲዮስ ወልዴ ያደረጋት ሙከራ እና ወንድወሰን ሚልኪያስ ከቅጣት ምት የሞከራት ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ፡፡
ሲዳማ ቡና 2-0 ወልዲያ
ጨዋታው እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች የታደመውና ደሲዳማ ቡና ፍፁም የበላይነት የታየበት ጨዋታ ተስተውሎበታል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች ለወልዲያ ተከላካዮች ፈተና ሆነው የዋሉ ሲሆን በተለይም ወንድማማቾቹ ባዬ ገዛኸኝ እና ሐብታሙ ገዛኸኝ እንዲሁም አዲሶቹ የውጭ ተጫዋቾቹ ኬኔዲ አሽያ ፣ አብዱለጢፍ መሀመድ እና ቤን መሀመድ ኮናቴ ከተመልካቹ አድናቆት የተቸረው እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡
በ14ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ ቤን ኮናቴ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ መከላከያን ለቆ ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ በአግባቡ ተጠቅሞ ሲዳማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ጫና ፈጥረው መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት ሲዳማዎች በ22ኛው ደቂቃ ደቡብ ፖሊስን ለቆ ሲዳማ ቡናን በተቀላቀለው ሐብታሙ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ በመግባት ኤሜሪክሪል ቢሌንጌ መረብ ላይ አሳርፎ ልዩነታቸውን ወደ ሁለት አስፍተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማዎች ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር እድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ወልዲያዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ ጨዋታው በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
የነገ መርሀ ግብር