የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ለተከታታይ አመት ለፍፃሜ ደርሰዋል፡፡
አርባምንጭ ከተማ 1-0 ፋሲል ከተማ
7:00 ሰአት ላይ በጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች አርባምንጮች የተሻሉ የጎል ዕድሎችን የፈጠሩ ሲሆን ፋሲል ከተማዎች ደግሞ ጠንካራ የመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ ክስተት የነበረው በ17ኛው ደቂቃ ላይ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው የፋሲሉ አማካይ ዳዊት እስጢፋኖስ ዳኛን በመሳደቡ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከተጠባባቂ ወንበር ላይ መወገዱ ነበር ።
በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በፋሲል ከተማ ላይ ማድረግ ችለዋል ። በተለይም ወንድሜነህ ዘሪሁን አሻምቶ ዮናታን ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ቴዎድሮስ በቀለ ያዳነበት ሙከራ አርባምንጭን ቀዳሚ ሊያደርግ የቀረበ አጋጣሚ ነበር ። በፋሲል ከተማዎች በኩልም አምሳሉ ጥላሁን በማሻማት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥሮ ነበረ ቢሆንም ፊሊፕ ዳውዝ ያገኘውን ግልፅ ዕድል አምክኖታል፡፡ በመጨረሻም መደበኛው የጨወታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ ወደ መለያ ምት ያመራሉ ተብሎ ቢጠበቅም አርባምንጭ ከተማዎች በ88ኛው ደቂቃ ላይ ወንድወሰን ሚልኪያስ ከራሱ ግብ ክልል በረጅሙ የላካትን ኳስ ወጣቱ አማካይ አለልኝ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር አርባምንጭ ከተማ ለፍፃሜ እንዲደርስ አድርጓል።
ሲዳማ ቡና 3-0 ወላይታ ድቻ
ከተያዘለት ጊዜ 20 ደቂቃዎች ዘግይቶ የጀመረው ጨዋታ የደርቢ ስሜትን ያስተናገደ እና በርካታ ተመልካች የታደመበት እንዲሁም ማራኪ እንቅስቃሴን ያየንበት ጨዋታ ነበር ፡፡
የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ የሲዳማ ቡና ፍፁም የበላይነት የታየበት ነበር፡፡ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ተፈሪ ከግራ መስመር በረጅሙ የላካትን ኳስ ጋናዊ የመሀል ተከላካይ ሚካኤህ አናን በማስቆጠር ሲዳማን ቀዳሚ ማድረግ ቻሉ፡፡ ሲዳማዎች በግቡ በመነቃቃት ተጨማሪ እድሎችን በፍፁም ተፈሪ ፣ ባዬ ገዛኸኝ እና አብዱለጢፍ አማካኝት መፍጠር ችለዋል፡፡ ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በበዛብህ መለዩ እና ጃኮ አራፋት አማካይነት ዕድሎችን ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ወላይታ ድቻዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ አጅግ ተሻሽለው ግብ ለማስቆጠር በርካታ ዕድልን ቢፈጥሩም ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ባሳዩት አስደናቂ ብቃት የበላይ መሆን ችለዋል፡፡ በ58ኛው ደቂቃ ላይ አበበ ጥላሁን በሰራው ያልተገባ አጨዋወት በሁለት ቢጫ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች በዛብህ መለዮ እና ያሬድ ዳዊት በ70ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጓቸው ሙከራዎች የግቡ ቋሚ በተመሳሳይ መልኩ መልሶባቸዋል፡፡ በ74ኛው ደቂቃ ላይ ታላቅ ወንድሙን ባዬ ገዛኸኝን ቀይሮ የገባው ሀብታሙ ገዛኸኝ አዲስ ግደይ በአስደናቂ ሁኔታ ተጫዋቾችን አልፎ ያቀበለውን ኳስ ከመረብ አሳርፎ የሲዳማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል፡፡ ከ 5 ደቂቃዎች በኃላም ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ፍፁም ተፈሪ በግንባሩ በመግጨት የሲዳማን መሪነት በሶስት ግቦች አስፍቶታል። ሲዳማዎች ተጨማሪ ግብ በአዲስ ግደይ አማካኝነት አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም በመሻሩ ጨዋታውን 3-0 በሆነ ውጤት ጨርሰዋል ።
መስከረም 13 ጅማሮውን ያደረገው የደቡብ ካስትል ዋንጫ በዚህ መልኩ የዐምና የፍፃሜ ተፋላሚዎቹን ሲዳማ ቡናን እና አርባምንጭ ከተማን ያገናኛል፡፡ 7:00 ላይ ለደረጃ ፋሲል ከተማ ከ ወላይታ ድቻ በ9:00 ሰአት ላይ ለዋንጫ ሲዳማ ቡና ከአርባምንጭ ከተማ በሀዋሳ ከተማ ስታድየም በሚያደርጉት ጨዋታም ይጠናቀቃል፡፡