ጋቦሮኒ ላይ በወዳጅነት ጨዋታ ኢትዮጵያን ያስተናገደችው ቦትስዋና ኢትዮጵያ 2-0 መርታት ችላለች፡፡ ቦትስዋና ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችበትን ቀን ለማክበር ታስቦ በተደረገው የወዳጅነት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ከእረፍት በፊት እና በኋላ ባስቆጠሯቸው ሁለት የፍፁም ቅጣት ምት ግቦች ጨዋታው አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ለመልቀቅ ያስቀገቡት ደብዳቤ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ተቀባይነትን ካጣ በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ባደረጉት ጨዋታ ሽንፈት ገጥሟቸዋል፡፡ በአንጻሩ የቀድሞ የጦር አመራር የነበሩት የቦትስዋናው አሰልጣኝ ዴቪድ ብራይት ዜብራዎቹን እየመሩ በወዳጅነት ጨዋታም ቢሆን ለመጀመሪያ ግዜ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ጄሮም ራማትልሃክዋኔ ባስቆጠረው ግብ ቦትስዋና መሪ ስትሆን የታውንሺፕ ሮለር የፊት አጥቂ የሆነው ራማትልሃክዋኔ በ67ኛው ደቂቃ አሁንም በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ግብ ቦትስዋናን አሸናፊ አድርጓል፡፡
ከሁለት አመት በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከቦትስዋና ጋር ለተመሳሳይ አላማ ባደረገው ጨዋታ 3-2 ማሸነፍ መቻሉ የሚታወስ ነው፡፡ በፊፋ የሃገራት ጨዋታ ፕሮግራም መሰረት ቦትስዋና ከናሚቢያ ጋር ለመጫወት ስትስማማ ኢትዮጵያ አሁንም የፊፋ ካላንደር መሰረት አድርጎ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ለማድረግ እየተሳናት ይገኛል፡፡
በጨዋታው ላይ የኢትዮጵያ የመጀመርያ 11 ይህንን ይመስል ነበር
ለዓለም ብርሃኑ
አብዱልከሪም መሃመድ፣ አስቻለው ታመነ፣ አንተነህ ተስፋዬ፣ ደስታ ዮሃንስ
ሙሉአለም መስፍን፣ ምንተስኖት አዳነ
ጋዲሳ መብራቴ፣ አብዱልራህማን ሙባረክ፣ ዳዋ ሆጤሳ
ጌታነህ ከበደ (አምበል)