የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የ2018ቱን የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ማስተናገድ ለሚፈልጉ ሃገራት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ባቀረበው ጥሪ መሰረት እስከቅዳሜ ድረስ ሶስት ሃገራት በጥር ወር የሚደረገውን ውድድር ለማስተናገድ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ካፍ እሁድ ይፋ እንዳደረገው ኢትዮጵያ፣ ሞሮኮ እና ኤኳቶሪያል ጊኒ ፍላጎት ያሳዩ ሃገራት ናቸው፡፡
ካፍ ኬንያን ከአስተናጋጅነት ካነሳ በኋላ ላለፈው አንድ ሳምንት ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ የውድድሩ አዘጋጅ ሊሆኑ እንደሚችሉ በርካታ መረጃዎች ቢወጡም ከሞሮኮ፣ ኢትዮጵያ እና ኤኳቶሪያል ጊኒ በስተቀር ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ያለው የአፍሪካ ሃገር ሊገኝ አልቻለም፡፡ ሞሮኮ የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ውድድርን ማስተናገድ የቻለች ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሃገር ስትሆን በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት እድል ቢሰጣትም በወቅቱ በተሰወኑ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት በተቀሰቀሰው የኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩን ከማስተናገድ እሯሷን አግልላለች፡፡
ኤኳቶሪያል ጊኒ በበኩሏ በ2015 ሞሮኮን ተክታ የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ የቻለች ሲሆን በ2012 በጣምራ ከጋቦን ጋር የአፍሪካ ዋንጫውን ማስተናገዷ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርብ አመታት የአህጉራዊ ውድድርን አስተናግዳ አታውቅም፡፡ በ2015 የዲኤስቲቪ ሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ያስተናገደችው ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1976 የአፍሪካ ዋንጫ ካስተናገደች በኃላ በ2001 የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ (በቀደሞ አጠራሩ የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ) ያስተናገደችው ትልቁ ውድድር ነው፡፡
ቀጣይ አዘጋጅ ሃገርን በ15 ቀን ውስጥ ይፋ እንዲረግ በጋና ርዕሰ መዲና አክራ በነበረው ስብሰባ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መወሰኑ ይታበሳል፡፡