የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለ12ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ድልድል በዛሬው እለት የተሳታፊ የክለብ ተወካዮች እና ጥሪ በተደረገላቸው እንግዶች ፊት በኢትየጵያ ሆቴል ተከናውኗል።
ስምንት ክለቦች በሚሳተፉበት ውድድሩ ከዚህ ቀደም ከመስከረም 20 እሰከ ጥቅምት 4 ድረስ ይከናወናል ተብሎ መርሀ ግብር ቢወጣለትም በዝናብ ምክንያት የአዲስ አበባ ስታድየም ለጨዋታ ምቹ አይሆንም በሚል ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 ድረስ ለማድረግ ፌደሬሽኑ እንደወሰነ አስታወቋል።
መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ በለጠ እንደገለፁት አዲስ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደጉ ክለቦችን ለማሳተፍ ፌደሬሽኑ ፈልጎ እንደነበረ እና ጥረቶችንም በማድረግ እንዲሳተፉ ስራዎችን መስራታቸው ያስታወቁ ሲሆን በሌሎች ጨዋታዎች ምክንያት እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል።
የእጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ከመከናወኑ በፊት ፌደሬሽኑ ለክለብ ተወካዮች የውድድሩን ደንብ በተመለከተ ገለፃ ያደረገ ሲሆን ሊሻሻሉ የሚገባቸው የውድድር ደንቦች ላይ ውይይት ተደርጓል። ውድድሩን የሚያሸንፉ ተጋባዥ ክለቦችን በተመለከተ የሽልማቱ ጉዳይ ላይ የደንብ መሻሻያ መደረጉ የተገለፀ ሲሆን ተጋባዥ የክልል ክለቦች ውድድሩን በአሸናፊነት የሚያጠናቅቁ ከሆነ ዋንጫ መውሰድ አለባቸው የሚል ጥያቄ ከክለቦች በመነሳቱ በድምፅ ብልጫ ፌደሬሽኑ ጥያቄውን ተቀብሎታል፡፡
ከውይይቱ በኃላ ኢትዮጰያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የምድብ አባት እንደሆኑ በመግለፅ የእጣ ማውጣት ስነስርአቱ የተከናወነ ሲሆን የሁለቱ ክለቦች የምድብ አባትነት ከደጋፊ ብዛት አንጻር የተሻለ የሜዳ ገቢ ለማግኘት እንደሆነ ተነግሯል።
የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች
እሁድ መስከረም 28 ቀን 2010
8:00 ደደቢት ከ አአ ከተማ
10:00 ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባ ጅፋር
ማክሰኞ መስከረም 30
9:00አዳማ ከተማ ከኤሌክትሪክ
11:00 ቅ/ጊዮርጊስ ከመከላከያ
ሁሉም ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲደረጉ የስታዲየም የመግቢያ ዋጋም ይፋ ሆኗል። ትሪቡን 150 ብር፣ ግራ እና ቀኝ ጥላ ፎቅ 100 ብር፣ ከማን አንሼ ወንበር ያለው 50 ብር፣ ከማን አንሼ ያለ ወንበር እና ካታንጋ 20 ብር፣ ሚስማር ተራ እና ዳፍ ትራክ 10 ብር እንደሆነ ፌዴሬሽነኑ አስታውቋል።