በደቡብ ክልል የከፍተኛ ሊግ ቡድኖችን ተካፋይ የሚያደርገው የካስቴል ዋንጫ ለ2ኛ ጊዜ በሆሳዕና ከተማ አስተነጋጅነት ከጥቅምት 11 ጀምሮ እንደሚካሄድ የደቡብ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከምድብ ሁለት 10 ክለቦች ተሳታፊዎች ያሉት የደቡብ ክልል በፌዴሬሽኑ አዘጋጅነት በየአመቱ አቋማቸውን የሚፈትሹበት የቅድመ ውድድር የሆነው የደቡብ ካስቴል የከፍተኛ ሊግ ዋንጫ ከጥቅምት 11 እስከ 24 በሆሳዕና ከተማ ይደረጋል፡፡ የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው አስቀድሞ ከሶስት አመታት በፊት ከክልሉ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ጋር በጋራ ይዘጋጅ የነበረውን ውድድር ከ2008 ጀምሮ የአንደኛ ሊግ ክለብን በመጋበዝ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የክልሉ የከፍተኛ ሊግ ተሳታፊዎች በመብዛታቸው ለብቻቸው ውድድር በማዘጋጀት ማካሄዳቸውን አስታውቋል፡፡
በውድድሩ ላይ ደቡብ ፓሊስ፣ ዲላ ከተማ፣ ሀላባ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ስልጤ ወራቤ፣ ካፋ ቡና፣ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ ሀምበሪቾ፣ ሚዛን አማን እና ቡታጅራ ከተማ ተሳታፊ ሲሆኑ ምናልባትት ፌዴሬሽኑ ይፋ ባያደርግም የፕሪምየር ሊግ ክለቦቹ ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ለመሳተፍ ጥያቄ ማቅረባቸውም ተሰምቷል፡፡