” የአሰልጣኙ የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ነው ” የህክምና ባለሙያዎች
” ማሰልጠን እችላለው ” ፖፓዲች
” አሰልጣኙን አላሰናበትንም፡፡ እረፍት ነው የሰጠነው” ኢትዮጵያ ቡና
” ኢትዮዽያ ቡና ከሌላ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ጋር እየተደራደረ ነው፡፡ ” ታማኝ ምንጮች
በኢትዮዽያ ቡና ታሪክ የመጀመርያ የውጭ ዜጋ አሰልጣኝ በመሆን በ2008 ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የመሩት ሰርቢያዊው የ72 አመት አዛውንት ድራጋን ፖፓዲች ከአንድ አመት በኋላ በድጋሚ ለ2010 የውድድር አመት አስቀድሞ በማምጣት የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸው ይታወቃል። አሰልጣኙ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ክለቡን እያዘጋጁ ባለበት ወቅት በድንገት ባጋጠማቸው ከፍተኛ የሆነ የልብ ህመም ምክንያት ቦሌ ወደሚገኘው አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል የገቡ ሲሆን በህክምና ባለሙያዎች ከፍተኛ ክትትል አድርገው ከሆስፒታል ወጥተው ትላንት በሲቲ ካፕ ኢትዮዽያ ቡና አአ ከተማን 4-1 ያሸነፈበት ጨዋታ እና ዛሬ በስታድየም በመገኘት ተመልክተዋል፡፡
የአሰልጣኝ ፖፓዲች የጤና ሁኔታ እየተሻሻለ ቢሆንም የህክምና ክትትል ያደረጉበት አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል እንዳሳወቀው ከሆነ በቂ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው እና ከፍተኛ ጫና ባለበት ስራ ላይ እንዳይሰማሩ አስገንዝቦ በድጋሚ ህመሙ የሚከሰት ከሆነ ከእድሜያቸው መግፋት ጋር ተያይዞ ለህይወታቸው አደጋ መሆኑን ለእሳቸውም ለክለቡም አሳውቋል ።
የጤንነታቸው ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑን ተከትሎ አሰልጣኙ ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ይለያያሉ የሚለው ዜና በርክቷል። ሶከር ኢትዮዽያ ከኢትዮዽያ ቡና እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ግን አሰልጣኙ እና ክለቡ እንዳልተለያዩ እና የጤንነታቸው ሁኔታ ጥሩ መሻሻል እስኪያገኝ ድረስ በቂ እረፍት እንዲያገኙ በማሰብ እረፍት ሰጥቷቸዋል፡፡ ከቡድኑ ጋር በጨዋታም ሆነ በልምምድ ወቅት ባይገኙም ባሉበት ሆነው ክለቡን እያገዙ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሆኖም ክለቡ ይሄን ይበል እንጂ ለክለቡ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንዳረጋገጥነው ከሆነ ከአሰልጣኙ የጤንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ ከመሆኑ እና የህክምና ባለሙያዎች ከሰጡት ጥቆማ ጋር ተደምሮ ኃላፊነቱን ላለመውሰድ በማሰብ በቅርቡ ከክለቡ ጋር ሊለያዩ እንደሚችሉ እየተነገረ ሲሆን እንዲያውም የክለቡ የቦርድ አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ ከአንድ ሰርቢያዊ አሰልጣኝ ጋር ተደራድረው በተወሰኑ ነገሮች ሳይስማሙ እንደቀሩ እና በሂደት በድርድር ሊስማሙ እንደሚችሉ መሰማቱ አሰልጣኙ እና የኢትዮዽያ ቡና ሊለያዩ የመቃረባቸውን ወሬ አጠናክሮታል።
አሰልጣኝ ፖፓዲች ዛሬ ወደ ክለቡ ፅህፈት ቤት በማቅናት “የጤናዬ ሁኔታ አያሳስባቹ፡፡ አሁን በጥሩ ሁኔታ እገኛለው፡፡ በሚገባ ቡድኑን ማሰልጠንም እችላለው፡፡” ማለታቸው ሲነገር ምናልባት ክለቡ ቅዳሜ ጠዋት ላይ በሚኖረው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ በአሰልጣኙ ቀጣይ እጣ ፈንታ ዙርያ ቁርጥ ያለ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአሰልጣኞች አሰለጣጠን መንገድ እስካልተቀየረ ድረስ ወደ ኢትዮዽያዊ አሰልጣኝ ዳግም ፊቱን እንደማያዞር የገለፀው ክለቡ በቀጣይ ከአሰልጣኝ ፖፓዲች ጋር ይቀጥላል ወይስ ሌላ አሰልጣኝ ከውጭ ያመጣል? አልያም አቋሙን በመቀየር በኢትዮዽያዊ አሰልጣኝ ይመራል? የሚለውን በቀጣይ ቀናት የምናገኘው መልስ ይሆናል።