የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የምድብ ለ ሁለተኛ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ሁለቱም ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡
09:05 ላይ የተጀመረው የመከላከያ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል፡፡ ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት መከላከያዎች በ16ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ አዳማ የግብ ክልል ተጠግተው የተፈጠረውን ግልጽ የሆነ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚ የተሻ ግዛው ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ በግምባር ተገጭቶ የግቡን አግዳሚ ሲገጭ የተመለሰውን ኳስ ወጣቱ በረከት ደስታ አግኝቶ ወደ ግብነት በመለወጥ አዳማን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከጎሉ በኋላ እስከ እረፍት ባሉት ደቂቃዎች የሚቆራረጡ ቅብብሎች እና ኢላማ የሌላቸው ተሻጋሪ ኳሶች የተበራከቱ ሲሆን በ45ኛው ደቂቃ ማራኪ ወርቁ ከተከላካዮች ሳጥን ውስጥ ለማስቆጠር አመቺ በሆነ አቋቋም ላይ ቢገኝም ወደ ግብ ከመምታት ይልቅ ለቡድን አጋሩ ለማቀበል ያደረገው ያልተሳካ ጥረት በመከላከያ በኩል የሚያስቆጭ የግብ እድል ነበር፡፡
ከሙከራው ጥቂት ሰኮንዶች በኋላ በግምት ከ30 ሜትር ርቀት የተገኘውን ቅጣት ምት የተሻ ግዛው በቀጥታ ወደ ግብ ሲመታ በአዳማ ተከላካዮች ተጨርፎ አቅጣጫውን በመቀየር ወደ ግብነት ተለውጦ የመጀመርያው አጋማሽ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የመጀመርያው አጋማሽ መልክን በያዘው ሁለተኛው አጋማሽ ከማዕዘን ከሚሻሙ እና ከሳጥን ውጪ ከሚመቱ ኳሶች ውጪ የሚጠቀስ የግብ አጋጣሚ በሁለቱም በኩል አልተፈጠረም፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ቴዎድሮስ በቀለ በግምባሩ ገጭቶ በግብ ጠባቂው ሲመለስበት በቀኝ መስመር የነበረው የተሻ ግዛው በቀጥታ ወደ ግብ መጥቶ በሽር ደሊል በጥሩ ሁኔታ ያወጣበት ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ የታየ ብቸኛው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር፡፡
ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ መከላከያ ከሁለት ጨዋታ 2 ነጥብ ሲይዝ አዳማ ከተማ 1 ነጥብ ይዞ በምድቡ ግርጌ ተቀምጧል፡፡ የአዳማ ከተማው ደሳለኝ ደባሽ ደግሞ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀለትን ዋንጫ ከቀድሞው የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አፈወርቅ አየለ እጅ ተቀብሏል፡፡
በማራኪ የቅብብል ዜማ ታጅቦ የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ የ11:30 ፍልሚያ እንደቀደመው ጨዋታ ሁሉ 1-1 ተጠናቋል፡፡ በአምናው የፍጻሜ ተፋላሚዎች መካከል የተደረገው ጨዋታም እስካሁን ከተደረጉት ጨዋታዎች የተሻለ ፉክክር ተስተውሎበታል፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባደረገበት የመጀመርያ አጋማሽ 8ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ አሉላ በግምባሩ ገጭቶ ግብ ለመሆን ቢቃረብም ሲሴይ ሀሰን ከመስመር ላይ ያወጣው ኳስ የመጀመርያው የጨዋታው አስደንጋጭ ሙከራ ነበር፡፡
በኤሌክትሪክ የሜዳ ክፍል አጋድሎ በቀጠለው የጨዋታ እንቅስቃሴ በ18ኛው ደቂቃ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል የሄደውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ጋናዊው ካሉሻ አልሀሰን ወደ ግብነት ለውጦ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከኤሌክትሪክ የመሪነት ጎል በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ የእንቅስቃሴ የበላይነት ቢኖረውም በማጥቃት ወረዳው ላይ እርጋታ የማይታይበት ሆኖ አምሽቷል፡፡ በሁለቱ የመስመር አጥቂዎች (አቡበከር እና ፎፋና) በኩል የሚነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችም በቀላሉ ሲመክኑ ተስተውሏል፡፡
እስከ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ድረስ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተሻጋሪ እና የቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት በመጨረሻ ፍሬ አፍርቶ ተቀይሮ በገባው አዳነ ግርማ የ89ኛ ደቂቃ የቡድኑን ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ተስፋ ያለመለመች ጎል በማስቆጠር ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ከጨዋታው ፍፃሜ በኋላ ዲዲዬ ሊብሬ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ የተዘጋጀለትን ሽልማት ከኢትዮጵያ እግርኳር ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ቾል ቤል እጅ ተቀብሏል፡፡