ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ለፍፃሜ ያለፈ ያልተጠበቀ ቡድን ሁኗል

የደቡብ አፍሪካው ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ባልተጠበቀ መልኩ የቱኒዚያው ክለብ አፍሪካን ከሜዳው ውጪ 3-1 በመርታት ለፍፃሜ መድረስ የቻለ ክለብ ሆኗል፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ 1-1 መለያየታቸውን ተከትሎ የማለፍ ቅድመ ግምቱ ለባለሜው ቢሰጥም ሱፐርስፖርት ዩናይትድ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ የፍፃሜ ተፋላሚዎች ውስጥ የሰሜን አፍሪካ ክለብ እንዳይኖር ያደረገበትን ወሳኝ ድል ቱኒዝ ላይ አግኝቷል፡፡ ድሉን ተከትሎም ሱፐርስፖርት በፍፃሜው ቲፒ ማዜምቤን የሚገጥም ይሆናል፡፡

ጨዋታውን በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመሩት ሱፐርስፖርቶች ቱሶ ፓላ ያሻገረለትን ብራድሊ ግሮብለር በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት በ16ኛው ደቂቃ እንቅዶቹን ሳይጠበቅ መሪ አድርጓል፡፡ ከእረፍት መልስ ቲቦሆ ሞኮኔ ያቀበለውን የተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ልማደኛው ኒው ዚላንዳዊው አጥዊ ጀርሚ ብሮኪ ኳስ እና መረብን አገናኝቶ 2-0 ሱፐርስፖርት በ53ኛው ደቂቃ መሪ መሆን ችሏል፡፡ ከሶስት ደቂቃ በኃላ የቀድሞ የኦሎምፒክ ማርሴ አጥቂ ሳብር ካሊፋ በፍፁም ቅጣት ምት ለክለብ አፍሪካ ሲስቆጥር ብሮኪ በ64ኛው ደቂቃ በስታዲየሙ የተገኘውን ደጋፊ ተስፋ ያስቆረጠ ግብ በማከል ሱፐርስፖርት 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡

ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ሳይጠበቅ በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ረጅም ርቀት መጓዝ ችሏል፡፡ ክለብ አፍሪካ በበኩሉ በግማሽ ፍፃሜው የተሰናበት ክለብ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በፊት ሌላኛው የቱኒዚያ ክለብ ኤትዋል ደ ሳህል ከአል አሃሊ ተሸንፎ ከቻምፒየንስ ሊጉ ወድቋል፡፡

ቲፒ ማዜምቤ እና ሱፐርስፖርት ዩናይትድ የመጀመሪያ ዙር የፍፃሜ ጨዋታቸውን ከሶስት ሳምንት በኃላ ሉቡምባሺ በሚገኘው ስታደ ቲፒ ማዜምቤ ያደርጋሉ፡፡ ቲፒ ማዜምቤ በ2016 የኮንፌድሬሽን ዋንጫን ማሸነፉ አይዘነጋም፡፡

የግማሽ ፍፃሜ ውጤቶች

ፋት ዩኒየን ስፖርት 0-0 ቲፒ ማዜምቤ (0-1)

ክለብ አፍሪካ 1-3 ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (2-4)

ፍፃሜ

ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ) ከ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (ደቡብ አፍሪካ) ጋር ለዋንጫ ይፋለማል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *