​የኦሮሚያ ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች ሲጠናቀቁ ሰበታ እና ጅማ አባ ቡና ለዋንጫ አልፈዋል

የኦሮሚያ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በሰበታ ከተማ ሜዳ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ጅማ አባቡና እና ሰበታ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ለፍፃሜ ዋንጫ አላፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

እንደጨዋታው ክብደት እና ለፍፃሜ አላፊ ቡድኖች እነማን እንደሆኑ ባለመታወቁ ምክንያት በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች በታደመመበት በዛሬው ሁለት ጨዋታ አስቀድመው 08:00 ላይ የተደረገው በቀድሞ የፕሪምየር ሊግ ተሳታፊዎቹ ሰበታ ከተማ እና ኢትዮዽያ መድን ተገናኝተው ሰበታ 2-0 አሸንፏል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች በዘጠና ደቂቃው የጨዋታ እንቅስቃሴ በኳስ ቁጥጥር ፣ ወደ ጎል በመድረስ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ያገኙትን የጎል አጋጣሚዎችን መጠቀም እና በመስመር የሚፈጥሩት የማጥቃት መንገድ የተሳካላቸው  ባለሜዳዎቹ ሰበታዎች በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው አብይ ቡልቲ አማካኝነት በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች አሸንፈው ወጥተዋል።

10:00 ላይ በቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ ጅማ አባቡና ለገጣፎ ለገዳዲን 1-0 አሸንፋል ። ጠንካራ ፉክክር በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአሰልጣኝ ያሬድ ቶሌራ የሚመራው ለገጣፎ በመጀመርያው አጋማሽ ከጅማ አባቡና በተሻለ ሁኔታ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ አጋጣሚ በመፍጠር የተሻለ የነበረ ሲሆን በተለይ አጥቂዎቹ ሀብታሙ ፈቀደ እና ፋሲል አስማማው ያገኙትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።

ከእረፍት መልስ አብዛኛውን የተጨዋች ለውጥ በማድረግ የገቡት አባቡናዎች ከመጀመርያው አጋማሽ ድክመታቸው ተሽለው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ኳስና መረብን የሚያገናኝ አጥቂ ባለመኖሩ ሲቸገሩ ተስተውሏል ። ጨዋታው ያለምንም ጎል ሊጠናቀቅ ይችላል ተብሎ ሲገመት የአባቡናው አምበል ጀሚል ያዕቆብ በግምት 25 ሜትር ርቀት አክርሮ በመምታት ግሩም የሆነ ጎል አስቆጥሮ ጅማ አባቡናን የፍፃሜ ጨዋታ አላፊ አድርጓል።

በጨዋታው ማብቂያ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ የጅማ አባቡናው ግብ ጠባቂ ቱንዴ አካንዴ  ኳስ ለመያዝ ዘሎ ሲወርድ ከመሬቱ ጋር ተጋጭቶ ምላሱን በመዋጡ በተጨዋቾቹና በስፖርት ቤተሰቡ ድንጋጤ የፈጠረ ቢሆንም የጅማ አባቡና ተጨዋቾች በተለይ ልደቱ ጌታቸው በፍጥነት በመድረስ ህይወቱን ለመታደግ ትልቁን ስራ የሰሩ ሲሆን ተጨዋቾች እና የህክምና ባለሙያዎች ተረባርበው ህይወቱን ሊያተርፉለት ችለዋል። ጨዋታውም በአባቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በውድድሩ ላይ በወጣው ደንብ መሰረት በነጥብ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የወጡ ቡድኖች ለዋንጫ የሚጫወቱ ሲሆን 3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁ ለደረጃ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ በዚህም መሰረት እሁድ 08:00 ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ኢትዮዽያ መድን ለደረጃ 10:00 ሰበታ ከተማ ከ ጅማ አባቡና ለዋንጫ የሚጫወቱ ይሆናል።

በመጨረሻም
የሰበታ ከተማ ሜዳ ለጨዋታ አመቺ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ቡድኖች ያቀረቡትን ቅሬታ በመቀበል ሜዳውን በፍጥነት ማስተካከል መቻሉ የዛሬ ጨዋታዎች በጥሩ ሁኔታ እንዲካሄድ አስችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *