[ሪፖርት – በለጠ ኤርበሎ ከ ሆሳዕና]
በ7 ክለቦች መካከል ከጥቅምት 19 ጀምሮ በሆሳዕና ከተማ ሲደረግ የቆየው የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ደቡብ ፓሊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ በመለያ ምት በማሸነፍ ለፍፃሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
7:00 ሰዓት ላይ የተጀመረው የደቡብ ፖሊስ እና ሀላባ ከተማ ጨዋታ መደበኛ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀው 1-1 ነበር፡፡ ሀላባ ከተማ ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውስጥ በስንታየሁ አሸብር ግብ ቀዳሚ መሆነ ቢችልም ብዙም ሳይቆይ በሀላባ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት አበባየሁ ዮሐንስ ወደ ግብ በመቀየር ደቡብ ፖሊስን አቻ አድርጓል፡፡ በጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር መደበኛው 90 ደቂቃ በአንድ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ በተሰጣቸው መለያ ምት ደቡብ ፖሊስ 3-2 በማሸነፍ ለእሁዱ ፍጻሜ ቀርቧል፡፡
9:00 ሰዓት ላይ በተጀመረው የሀዲያ ሆሳዕና እና የቤንች ማጂ ቡና ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ታይቶበት መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡ በተሰጡት የመለያ ምቶችም እያንዳንዳቸው ከተሰጣቸው ሰባት መለያ ምቶች ሀዲያ ሆሳዕና አምስቱን ሲያስቆጥር ቤንች ማጂ ቡና አራት አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዲያ ሆሳውና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የሀዲያ ሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ማቲዎስ ሰለሞንም ሦስት መለያ ምቶችን በማዳን ክለቡን ወደ ፍፃሜው ጨዋታ በመምራት ኮከብ ሆኖ አምሽቷል፡፡
የደቡብ ካስቴል ዋንጫ የፊታችን እሁድ ጥቅምት 26/2010 የሚጠናቀቅ ሲሆን ከፍፃሜው ጨዋታ አስቀድሞ ሀላባ ከተማ እና ቤንች ማጂ ቡና ቀን 6:00 ሰዓት ላይ ለደረጃ ይጫወታሉ፡፡ ለዋንጫ ደግሞ 08:00 ላይ አዘጋጁ ሀዲያ ሆሳዕና ከደቡብ ፖሊስ የሚጫወቱ ይሆናል፡፡