በ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከምድቡ አንደኛ በመሆን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ፋሲል ከተማን አስተናግዶ የያዘውን የሁለት ጎል መሪነት ማስጠበቅ ሳይችል ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡
በርካታ የጎንደር እና የአዲግራት ከተማ የስራ አመራሮች በተገኘበት በዚህ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የማስታወሻ ልውውጥ አድርገዋል፡፡ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊትም በቅርቡ ህይወታቸው በድንገት ያለፈው የቀድሞ የወልዋሎ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ገ/ፃዲቅን በማሰብ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡
በባለሜዳው የወልዋሎ ደጋፊዎች እና ከጎንደር ቡድናቸውን ለመደገፍ በተገኙት የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች መልካም ድባብ የተጀመረው ጨዋታ ግበ ለማስተናገድ የፈጀው ጥቂት ደቂቃዎች ነበሩ፡፡ በ4ኛው ደቂቃ ላይ መኩሪያ ደሱ በሁለት ተጫዋቾች መሀል ያሾለከውን ኳስ ከድር ሳሊህ ተቆጣጥሮ ወደግብ ሲመታ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት አዲሱ ፈራሚ ሙሉአለም ጥላሁን በአግባቡ በመጠቀም ወልዋሎን ቀዳሚ አድርጓል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ ፋሲል ከተማዎች ወደ ጨዋታው በፍጥነት ለመመለስ ተቸግረው ታይተዋል፡፡ በቀጣዮቹ 15 ደቂቃዎችም የተደራጀ እንቅስቃሴ ሳይታይበት ዘልቋል፡፡ በ19ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ቅጣት ምት አብዱራማን ሙባረክ ወደ ግብ አክርሮ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ በግሩም ሁኔታ ያመከነው ኳስ የፋሲል የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡
አንድ ጊዜ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለ የቀጠለው ጨዋታ በ10 ደቂቃ ልዩነት ወልዋሎዎች ካደረጉት ሙከራ ውጪ የሚጠቀስ አጋጣሚ አልተፈጠረም፡፡ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ከድር እና ሙሉዓለም በ32ኛው እና 40ኛው ደቂቃ የፋሲልን በር ሲፈትሹ በ45ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉዓለም ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ ያሻገረለትን ኳስ ከድር ሳሊህ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመለወጥ የመጀመሪያው አጋማሽ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 2-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በተለይ እንግዶቹ በድንቅ ሁኔታ ከ2-0 ተመሪነት ወደ አቻ የተሸጋገሩበት ክፍለ ጊዜም ነበር፡፡ በ62ኛው ደቂቃ ያስር ሙገርዋ ወደ ግብ አክርሮ የመታውን ኳስ በረከት ወደ ውጪ በማውጣቱ የተገኘውን የማዕዘን ምት በመጠቀም ፋሲሎች በሰዒድ ሀሰን ጎል ልዩነታቸውን ማጥበብ ችለዋል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኃላ ወልዋሎች መሪነታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት የተለያዩ የሰአት ማባከኛ ዘዴዎች ሲጠቀሙ ተስተውሏል፡፡ በዚህም ምክንያት የፋሲል ተጫዋቾች የወልዋሎዎች ድርጊት አግባብ አይደለም በሚል ከመሀል ዳኛው ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ሲገቡ ተስተውሏል፡፡
ፋሲል ከተማ ጨዋታው ወደ ማገባደጃው በገፋ ቁጥር የአቻነት ጎል ለማግኘት ጥረታቸውን አጠናክረዋል፡፡ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ፊሊፕ ዳውዝ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ኤፍሬም ደርሶ ያዳነበትም የመጠቀስ የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ ነበር፡፡ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ላይ የተገኘውን ማዕዝን ምት ዓይናለም ኃይለ ወደ ግብነት ለውጦ የማታ ማታ ፋሲልን ነጥብ ያጋራች ወሳኝ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡
በጎሉ መቆጠር ከፍተኛ የደስታ ስሜት ውስጥ የገቡት የፋሲል ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ የቡድን አባላት ወደ ሜዳ ገብተው ደስታቸውን ሲገልፁ የተስተዋለ ሲሆን ከዚህ ክስተት በኋላ በስታድሙ መሀለኛ የመቀመጫ ክፍል (ካታንጋ) በተነሳ ግጭት የድንጋይ መወራወሮች ተስተውለዋል፡፡ ጥቂት የፋሲል ደጋፊዎች የመፈንከት አደጋ ሲደርስባቸው የጸጥታ አካላት ሁኔታው የከፋ ደረጃ ሳይደርስ ሊያረጋጉት ችለዋል፡፡
ጨዋታው በዚህ ክስተት ለ6 ደቂቃዎች ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ ተጀምሮ ብዙም ሳይቆይ የተጠናቀቀ ሲሆን የሁለቱም ቡድን የደጋፊ ተወካዮች ሰላምታ ተለዋውጠው በሰላም ተለያይተዋል፡፡