በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ሳምንት ሀዋሳ ከተማ ወልዲያን አስተናግዶ 4-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ዳዊት ፍቃዱ የውድድር አመቱ የመጀመርያ ሐት-ትሪክ ሰርቷል፡፡ አምና በደደቢት ጥሩ ያልሆነ ጊዜ ያሳለፈው ዳዊት በአዲሱ ክለቡ ድንቅ አጀማመር ማድረግም ችሏል፡፡ ዳዊት ስለ አዲሱ ክለቡ፣ ስለ ሐት-ትሪኩ እና የውድድር ዘመን እቅዱ ከቴዎድሮስ ታከለ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሊጉን በሽንፈት ብትጀምሩም በሁለተኛው ሳምንት ቡድናችሁ በአንተ ሐት-ትሪክ ታግዞ ጣፋጭ ድል አስመዝግባችኀል…
” ሊጉን በሽንፈት ነበር የጀመርነው፡፡ ሆኖም በጅማ አባ ጅፋር ብንሸነፍም ውጤቱ እንቅስቃሴያችንን የሚገልጽ አልነበረም፡፡ በመጨረሻው ደቂቃ ግቦች አስተናግደን በራሳችን ድክመት ነው የተሸነፍነው፡፡ በሜዳችን ያደረግነውን ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ደግሞ በእንቅስቃሴ የበላይ በመሆን ጭምር አሸንፈናል፡፡ እኔም ሶስት ጎል አስቆጥሪያለው ፤ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡”
” አስቀድሜ ክለቡን ስመርጥ ክለቡ የራሱ አጨዋወት ያለው እና በቡድኑ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች የጥራት ደረጃ እዚህ ክለብ ሳልመጣም አውቃለው፡፡
” በቡናም ሆነ በደደቢት እያለው ከአምና ውጭ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ውስጥ ነበርኩ፡፡ እሱም ያው ከክለቡ ጋር በነበረኝ የግል ቅራኔ ምክንያት ነበር፡፡ እስከ አሁን በፕሪምየር ሊግ መጫወት ከጀመርኩ አንስቶ በተፎካካሪነት ውስጥ ነበርኩኝ፡፡ በወልዲያው ጨዋታ ያሳየውት ብቃት ግን በቀጣይ የተሻልኩ እንድሆን ሞራል እና ስንቅ ነው የሚሆነኝ፡፡ ክለቡንም የተሻለ ቦታ አደርሳለው ብዬም አስባለሁ፡፡”
ከደደቢት ጋር የነበረህ ያለፈው አመት ውዝግብ እና ጉዳቶችን ተከትሎ በርካታ ጨዋታ ያለማድረግህ እንዲሁም ከግብ ርቀህ መቆየትህ ምን ያህል ተፅህኖ አድርጎብሀል?
አምና በተለያዩ ችግሮች ምክንያት አዕምሮዬ ጥሩ አልነበረም፡፡ ኳስ ደግሞ የአዕምሮ ነፃነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ኳስን ነፃ ሆነ ስትጫወት እና ተረብሸህ ስትጫወት እጅግ ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ አምና በኔ እና በደደቢት መካከል በነበረው ክፍተት ጥሩ ስሜት አልነበረኝም፡፡ እንደዛም ሆኜ የቀነስኩት ነገር የለም፡፡ እንደውም የተሻሻልኩበት ጊዜ ሆኖልኛል፡፡ ከዚህም በተሻለ መልኩ የተሻልኩ ሆኜ የምገኝ ይመስለኛል፡፡
ከአዲሱ ክለብህ ጋር ምን አቅደሀል?
ወደዚህ ክለብ ስመጣ ከቡድን ጓደኞቼ ጋር በመሆን ዋንጫ ማንሳት ነው አላማዬ፡፡ ይህ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ዋንጫ ማንሳት ካልቻልን እንኳን ከ1-3 ያለውን ደረጃ ይዞ ማጠናቀቅ እፈልጋለው፡፡ የክለቡን የቀደመ ታሪክ ዘንድሮ ብንመልስ ደስ ይለኛል፡፡
በርካታ ጊዜያትን በሊጉ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ብትፎካከርም ከጫፍ ደርሰህ ሳታሳካ ቀርተሀል፡፡ ዘንድሮስ?
” ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ለመጨረስ አላማውና እቅዱ አለኝ፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ ሀገር የተወሰኑ አጥቂዎች ናቸው ይህን ክብር የሚያገኙት፡፡ አጥቂዎች አያስቆጥሩም ይባላል ፤ ነገር ግን ኳስን የሚያቀርቡ አማካዮች ከሌሉ አጥቂው ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ዘንድሮ ግን ባለሁበት ክለብ ውስጥ የመጨረሻ ኳስ የሚያቀርቡ እና የተሻለ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች አሉ፡፡ እናም ያንን ተጠቅሜ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኜ ማጠናቀቅ እፈልጋለው፡፡
የብሔራዊ ቡድን ቦታህን ዳግም የማግኘት አላማህስ?
ለብሔራዊ ቡድን ለመመረጥ አሁንም ጠንክሬ እሰራለው፡፡ ከዚህ ቀደም ለረጅም ጊዜያት ብሔራዊ ቡድን ላይ አገልግያለሁ፡፡ ሆኖም አሁን ያለው ብሔራዊ ቡድን የተረጋጋ አይደለም፡፡ በሰውነት ቢሻው አሰልጣኝነት ዘመን ይበልጥ የምንተዋወቅ ነን፡፡ ለረጅም አመታት ከአንድ ሁለት ተጫዋቾች ውጭ በርካቶቻችን ብዙ ጊዜ አብረን የቆየን ነበርን፡፡ የተወሰኑ ብቻ እንዳልኩት ይጨመራሉ ፤ ጥንካሬውንም ይዞ ለረጅም ጊዜ ሊዘልቅ የቻለው በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ከዛ በኃላ ያለው ብሔራዊ ቡድን ግን የተጫዋቾች ሞርጫው ወጥ ያልሆነ በመሆኑ እርስ በርስ ሊተዋወቁ የማይችሉ ተጫዋቾች ነው የሚሰበሰቡት፡፡ ይህ ደግሞ በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት ተፅዕኖ አምጥቷል፡፡ ህዝቡም እንዲከፋ አድርጓል፡፡ በሌሎች ሀገራት የአንድ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ለረጅም አመት አብሮ ይዘልቃል፡፡ ባሉት ላይ ትንሽ ለውጥ ብቻ ነው የሚደረገው፡፡ ያ ነገር ብሔራዊ ቡድናቸው ጠንካራ እንዲሆን ያደርጋቸዋል፡፡ እኛም ይህን መንገድ ብንከተል ባይ ነኝ፡፡ እኔም ከአሁን በኋላ ወደ ብሔራዊ ቡድን ተመልሼ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፡፡