የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን በ2018ቱ የአፍሪካ ሃገራት ሻምፒዮና (ቻን) የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተደልድሎ በመጀመሪያው ጨዋታ 5-1 ከተሸነፈ በኋላ የመልሱን ጨዋታ ሳያደርግ ራሱን ከውድድሩ ማግለሉን ተከትሎ በአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ቅጣት ተጥሎበታል።
ዛሬ በሞሮኮ ራባት የተሰበሰበው የቻን አዘጋጅ ኮሚቴ የውድድሩን ደንብ አንቀፅ 59 በመጥቀስ በጅቡቲ እና ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር ከነበራት ጨዋታ በፊት ራሷን ያገለለችው ጋቦን ላይ የ10,000 ዶላር ቅጣት አስተላልፏል። ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪ ሁለቱ ሃገራት በ2020 ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች ተብሎ በሚጠበቀው የቻን ውድድር ላይ እንዳይሳተፉ ከማጣሪያ ውጪ ይሆናሉ። የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያውን ጨዋታ በሃገሩ ካስተናገደ በኋላ ለመልሱ ጨዋታ ወደ አዲስ አበባ ሳይጓዝ በመቅረቱም የሃገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተጨማሪ የ10,000 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ተወስኖበታል።
ዋልያዎቹ ምንም እንኳን ጅቡቲን ማለፍ ቢችሉም በመጨረሻው ዙር በሱዳን፣ እንዲሁም ካፍ በድጋሚ በሰጣቸው ዕድል በሩዋንዳ ተሸንፈው ከውድድሩ መቅረታቸው ይታወሳል።