ሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ በኬንያ ከህዳር 24 ጀምሮ የሚስተናገድ ሲሆን 10 ሀገራት የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡ የምድብ ድልድሉም ዛሬ ይፋ ሆኗል፡፡ ሁለት ተጋባዥ ሃገራት እና ሰባት የሴካፋ ዞን አባል ሃገራት በውድድሩ ላይ ሲሳተፉ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከወቅቱ ቻምፒዮኗ ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩንዲ እና ተጋባዥ የሆነችው ዚምባቡዌ ጋር ተመድባለች፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ሰኞ ህዳር 25 ከቡሩንዲ ጋር 8፡00 ሰዓት የምታደርግ ይሆናል፡፡
የሴካፋ ዋና ፀሃፊ ኒኮላስ ሙሶንዬ እንደጠቀሱት ጨዋታዎቹ በታንዛኒያው የስፖርት ቴሌቪዥን ጣቢያ አዛም የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኛሉ፡፡ እንዲሁም አዛም ቲቪ እስከ2019 የሴካፋ ውድድርን በቀጥታ ስርጭት ለመሸፈን ከስምምነት ደርሷል፡፡
ዚምባቡዌ ከነፃነት በኃላ ለረጅም ግዜ በስልጣን የቆዩትን ሮበርት ሙጋቤ በጦር ኃይሉ አስገዳጅነት ከስልጣን እንዲወርዱ በሳምንቱ መጀመሪያ መደረጉ በሃገሪቱ የፓለቲካ ትኩሳት እንዲቀሰቀስ አድርጓል፡፡ ሆኖም በዋሊያዎቹ ምድብ የሚገኙት ዚምባቡዎች በሴካፋ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡
በምድብ አንድ አዘጋጇ ኬንያ፣ ሊቢያ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ በአንድ ላይ የተደለደሉበት ጠንካራው ምድብ ሆኗል፡፡ ከየምድብ ሁለት ሃገራት ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፍ ይሆናል፡፡ ጨዋታዎቹ በካካሜጋ፣ ኪሲሙ እና ናኩሩ ስታዲየሞች የሚስተናገዱ ይሆናሉ፡፡
ምድብ አንድ
ኬንያ ፣ ሩዋንዳ ፣ ሊቢያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ዛንዚባር
ምድብ ሁለት
ዩጋንዳ ፣ ዚምባቡዌ ፣ ቡሩንዲ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን
የኢትዮጵያ ጨዋታዎች
ሰኞ ህዳር 25
ቡሩንዲ ከ ኢትዮጵያ (8፡00)
ዓርብ ህዳር 29
ደቡብ ሱዳን ከ ኢትዮጵያ (8፡00)
እሁድ ታህሳስ 1
ኢትዮጵያ ከ ዩጋንዳ (10፡00)
ማክሰኞ ታህሳስ 3
ዚምባቡዌ ከ ኢትዮጵያ (10፡00)
ፎቶ፡ ከኬንያዊው ጋዜጠኛ ዴቪድ ኩዋሊምዋ